‎ለ36 ሺህ ሰዎች የገበያ ዕድል የሚያሰፋው የማር ኤግዚቢሽን በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።

1

‎የማር እና የንብ እርባታ ተያያዥ ምርቶችን ለማስተዋወቅ፣ የወጣት ኢንተርፕራይዞችን የገበያ ዕድል ለማስፋት እና ከገዢዎች ጋር ቀጥተኛ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የማር የንግድ ትርዒት እና ኤግዚቢሽን በደሴ ከተማ ተከፍቷል ።
‎
‎የማር ኤግዚቢሽኑ ባዛር ዋና ዓላማ በአመልድ ኢትዮጵያ አቀስታ ክላሰትር እና ፒኤቺኢ ኢትዮጵያ ደብረብርሃን ክላስትር ስር ባሉ ወረዳዎች በንብ እርባታ እና በማር ምርት የተሰማሩ ወጣት ኢንተርፕራይዞች እና ንብ አናቢዎች ከነጋዴዎች እና ከጅምላ ገዢዎች ጋር ማገናኘት ነው።
‎
‎የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው እንደዚህ አይነት ፕሮጀክቶች ለከተማዋ እጅግ ጠቃሚ እና ወሳኝ በመኾናቸው እንደሚበረታቱ አስታውቀው የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ ሊደገፉ ይገባቸዋል ብለዋል።
‎
‎የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም በበኩላቸው በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ንብ አናቢዎች ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው ለጤና ጠቃሚ የኾነ ንጹህ ማር ለማግኘት መሰል ኤግዚቢሽኖች ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል።
‎
‎በአመልድ ማያ ፕሮግራም አቀስታ ክላስተር አስተባባሪ ጓንጉል ተገኝ፣ በደቡብ ወሎ ዞን የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋት፣ በንብ እርባታ የተሰማሩ ወጣት ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር እና የገበያ ትስስርን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።፡
‎
‎አስተባባሪው 88 ሺህ ሰዎች በተለያየ ሙያ ሥልጠና እና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ በመኾን ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል። በዚህ ሥራም 36 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።
‎
‎በኤግዚቢሽኑ ምርቶቻቸውን ከሁሉም ወረዳ ያመጡ ንብ አናቢዎች እና የማር ምርት አቅራቢዎች በማያ ፕሮግራም ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸው ይህ ባዛር እና ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥርላቸው አስታውቀዋል።
‎
‎በአመልድ ኢትዮጵያ ማያ ፕሮግራም ወጣቶች በንብ እርባታ፣ በማር ምርት፣ በበግ እና ፍየል ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ እና በሌሎች ዘርፎች ጭምር ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እየተሠራ ይገኛል።
‎
‎#የመደመር_መንግሥት!
‎
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
‎
‎#ደሴ #ኅዳር_11_2019_ዓ_ም
‎
‎✍️በሳሙኤል ኪሮስ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎1 ሺህ 793 ኢንቨስትመንቶች ወደ ሥራ የገቡበት ሰሜን ሸዋ ዞን የእመርታ ጉዞ 🏭