
”ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም።”
ይህ ሃሳብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የህልውና ቃል ኪዳን፣ የነፃነት ማህተም እና የሀገር ፍቅር የመጨረሻው ጥግ መግለጫ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ ትሠራለች፤ በልጆቿ አጥንት እና ደም ትጸናለች ያሉት።
እናት ሀገር በካርታ ላይ የተሳለች ተራ መሬት ሳትኾን ከጥንት ጀምሮ አጥንት ተከስክሶላት፣ ደም ተንቆርቁሮላት፣ ስፍር ቁጥር የሌለው የጀግኖች ህይወት ተገብሮላት የታነጸች የክብር መቅደስ መኾኗን በጉልህ ያትማል።
የአባቶቻችን ደም ለዚህች ምድር ዝም ብሎ የፈሰሰ ሳይኾን የነፃነቷ መሰረት፣ የሉዓላዊነቷ ዋልታ እና የማንነቷ ጠንካራ ማገር ነው።
በየዘመናቱ የተነሱ ወራሪዎች የሀገሪቱን ክብር ለማዋረድ ቢሞክሩም ያ የነፃነት አደራ በየልቡ ውስጥ እያስተጋባ “የደፈረሽ ይውደም!” በሚል በማያወላዳ የቁርጠኝነት መንፈስ ጠላትን አሳፍሮ መልሷል።
እናት ኢትዮጵያን መድፈር ወይም ህልውናዋን መፈታተን፣ በሕይወት ካሉት ልጆቿ ጋር ብቻ መዋጋት አይደለም። ለክብሯ ሲሉ በየጦር ሜዳው ከወደቁት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰማዕታት አፅም እና መንፈስ ጋር መጋፋት ነው።
”የደፈረሽ ይውደም” የሚለው እርግማን እና ጸሎት የተጣመረበት ሃሳብም የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስደፈር ማንም ኀይል አቅም እንደሌለው የሚያስጠነቅቅ የነበልባል ድምጽ ነው። ቢሞክርም እጣ ፈንታው ፍጹም ውድመት መኾኑን ያውጃል። ይህ ጥልቅ ስሜት ዛሬም ድረስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የሕዝቡ የጋራ የልብ ትርታ ነው።
ኢትዮጵያ የተከበረችው በውል፣ በልመና ወይም በስጦታ ሳይኾን በማይነጥፈው የጀግኖች ደም እና አጥንት በመኾኑ የፈሰሰውን ደም አክብሮ ሀገርን በሉዓላዊነት የማስቀጠል አደራ የዘመኑ ትውልድ ሊሸከመው የሚገባ የተቀደሰ ታሪካዊ ግዴታ ነው።
✍️ በስማቸው አጥናፍ
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
Ameco #BloodCovenant #PriceOfFreedom
#EthiopiaSovereignty
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
