
የአማራ ክልል መንግሥት ለአዳሪ ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
በክልሉ ወደ ሥራ የገቡ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ባለፉት ዓመታት የተሻሉ ተማረመዎችን ሲያፈሩ በተግባር ተስተውለዋል።
የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን ሥራ መጀመርን የአካባቢው ተማሪዎች በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
በሰቆጣ ከተማ አዝባ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አሰፉ ታደለ እና ተማሪ አማኑኤል አዳነ እንዳሉት ለትምህርት ወጭ ከወላጅ በየወሩ እስከ ሦሥት ሺህ ብር ያስቸግራሉ።
ይህን ገንዘብም ለመጠየቅ ሁሌም እንደሚሳቀቁ እና ሁሌም ሃሳብ ውስጥ ስለሚኾኑ በትምህርት አቀባበላቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ተማሪዎቹ አሁን ላይ ግን በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ተስፋ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።
የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን የመማር ማስተማር ለማስጀመር እየተደረገ ያለው ጥረትም እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙት መርሐ ግብሮች መካከል የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት አንዱ ሲኾን ለዚህም የክልሉ መንግሥት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ይገኛል።
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የኾነው የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይም በጀት ተመድቦለት ግንባታው መጠናቀቂያው ላይ ነው የሚገኘው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱን ወደ መማር ማስተማር ሥራው ለማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ለዚህም ትምህርት ቢሮው የሰው ኀይል ማሟላት፣ የመምህራን ቅጥር እና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ወደ ትምህርት ቤቱ ገብተው የሚማሩ ተማሪዎችን የመለየት ሥራ እንደተሠራም ጠቁመዋል። የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመርም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ ማስተማር ሲጀምርም በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ለመግባት የሚያደርጉትን ፉክክር እንደሚያጠናክርም ነው ያስረዱት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
