
ሐይቅ እና ወንዝ ያለው ማኅበረሰብ ሃብት እና ሲሳይ አለው። ይህ ሃብትም የሕይወት መሠረት ይኾናል። ከውኃ ውስጥ የሚገኘው ዓሣም የምግብ ምንጭ ብቻ ሳይኾን የገቢ፣ የሥራ ዕድል እና የኢኮኖሚ አቅም ነው።
በሐይቆች፣ በወንዞች እና በግድቦች የታደለው የአማራ ክልልም ይህን የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ምርት እና የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለመቀየር እየሠራ ይገኛል። የአማራ ክልል ለዓሣ ምርት ምቹ የኾኑ ሐይቆች እና ወንዞች ያሉት ክልል ነው። ይህን ሰፊ የውኃ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለክልሉ ከፍተኛ የምርት እና የኢኮኖሚ አቅም ሊኾን ይችላል።
አማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ የዓሣ ግብርና ባለሙያ አበበ ፈንታሁን በተፈጥሮ የክልሉ ሐይቆች እና ወንዞች ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ቶን የሚጠጋ ዓሣ የማምረት አቅም እንዳላቸው ተናግርዋል። በባለፈው በጀት ዓመት ከ43 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ለገበያ መቅረቡን የሚገልጹት ባለሙያው በዚህ ዓመት ደግሞ ዘመናዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ እስከ 52 ሺህ ቶን ለማምረት መታቀዱን አስረድተዋል።
የዓሣ ምርት በተፈጥሮ ሐይቆች እና ወንዞች ብቻ እንዳይወሰን ለመስኖ እና ለእንስሳት መጠጥ የተገነቡ ግድቦችን ወደ ዓሣ ምርት ማስገባት ተጀምሯልም ነው ያሉት። በክልሉ ወደ 40 የሚጠጉ ግድቦችን ለዓሣ ምርት ለማዋል እየተሠራ ነው። በዚህ ዓመት በ30 ግድቦች ላይ የዓሣ ጫጩት የመጨመር ዕቅድ ተይዟል ብለዋል። ይህም ለተለያዩ ዓላማዎች የተገነቡ የውኃ አካላትን ተጨማሪ የምርት ምንጭ ለማድረግ የተያዘ አዲስ አቅጣጫ መኾኑን አስገንዝበዋል።የዓሣ ምርትን ለማሳደግ ከተያዙት ዋና ዋና አቅጣጫዎች አንዱ የኩሬ ዓሣ ግብርና ነው።
በተፈጥሮ ከውኃ አካላት ርቀው የሚኖሩ አርሶ አደሮችም በዓሣ ምርት እንዲሳተፉ የኩታገጠም ኩሬ ግብርና እየተስፋፋ ነው። በዚህ ዓመትም 3 ሺህ 200 አርሶ አደሮችን በዓሣ ግብርና ለማሳተፍ ታቅዷል። 312 አርሶ አደሮች ኩሬ በማዘጋጀት የዓሣ ጫጩት ወደ ማሳደግ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት።
ይህ አርሶ አደሮች ከእርሻ ሥራቸው በተጨማሪ አዲስ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ እና ለቤተሰቡ የምግብ አማራጭ እንዲፈጥር ዕድል ይከፍታል ነው ያሉት። ዓሣን ማምረት አንዱ ሥራ ቢኾንም በጥራት ለተጠቃሚው ማድረስ ደግሞ ሌላው ፈተና ነው፤ በዚህ ረገድ የዓሣ ማቀነባበሪያ ማዕከላትን፣ የመሸጫ ሱቆችን እና ቀዝቃዛ ማከማቻዎችን ማስፋፋት በትኩረት እየተሠራበት መኾኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ወጣቶችን በዓሣ ማስገር እና በዘርፉ ተያያዥ ሥራዎች በማሳተፍ የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ የሥራ ዕድል የመፍጠር ጥረቶችም እየተደረጉ መኾናቸውን አብራርተዋል። የአማራ ክልል የዓሣ ሀብት ከሐይቆች እና ከወንዞች የሚገኝ ተፈጥሯዊ ስጦታ ብቻ አይደለም፤ በግድቦች፣ በኩሬዎች እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ሊያድግ የሚችል የኢኮኖሚ አቅም ነው። ይህ ሀብት በዘላቂነት ከተጠበቀ እና በተገቢው ሁኔታ ከለማ፣ የዛሬው የውኃ ስጦታ የነገው የብልጽግና መሠረት ሊኾን ይችላል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
