የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ከፍታ፤ የቢሾፍቱ ሜጋ ፕሮጄክት እና የኢኮኖሚ አቅም

9
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚለካው በወረቀት ላይ በተቀመጡ ወይም በተጻፉ ዕቅዶች ብቻ አይደለም። የእውነተኛ ዕድገት ትክክለኛ ማረጋገጫው በዜጎች ዕለታዊ ሕይወት ላይ በሚፈጥሩት ተጨባጭ የምርት ዕድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የገቢ መሻሻል ጭምር እንጅ።
በመደመር መንግሥት የተጠነሰሰው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ዛሬ በተግባር የሚታይ እና የሚጨበጥ እውነት ኾኗል። የመደመር መንግሥት የሰው ኃይል አቅምን፣ የቴክኖሎጅ ዕውቀትን እና ሀገራዊ ሀብትን በማቀናጀት ኢትዮጵያ ከነበረችበት የድህነት ማነቆ ማላቀቅ የሚያስችሉ ዘመን ተሻጋሪ ልማቶችን እያከናወነ ይገኛል።
በተያዘላቸው ጊዜ በተበጀተላቸው ወጪ፣ በጥራት እና በፍጥነት የሚጠናቀቁ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጄክቶችም የሀገራችንን አዲስ የመፈጸም አቅም እና የሥራ ባሕል ቁልጭ አድርገው እያሳዩ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጄክቶችን ማለም እና መጀመር ብቻ ሳይኾን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና ጥራት አጠናቅቆ ለሕዝብ ጥቅም ማዋል እንደምትችል በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች ብለዋል።
ይህ መልዕክት የሀገሪቱን አዲስ የመፈጸም አቅም እና የማይበገር ሀገራዊ የራስ መተማመንን የሚያንጸባርቅ ነው። ለዚህ ተግባራዊ ዕድገት አንዱ ግልጽ ማሳያ በዓመት ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኘውን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ በላቀ ደረጃ ለማስፋት የተጀመረው ጥረት ነው። በ2018 ዓ.ም በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለዚህ አዲስ ምዕራፍ ተጠቃሽ ማረጋገጫ ነው።
ፕሮጄክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲኾን የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የማስተናገድ አቅምን ከሁለት እጥፍ በላይ የማሳደግ አቅም እንዳለው ተገልጿል። ይህ ግዙፍ የአቪዬሽን ፕሮጄክት ከትራንስፖርት ዘርፍ ባሻገር ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በግንባታው ወቅትም ኾነ ከአገልግሎት መስጠት በኋላ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ዘላቂ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋና የአቪዬሽን እና የቱሪዝም መግቢያ በመኾን የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በእጥፍ ያሳድገዋል። የንግድ እና የሎጀስቲክስ እንቅስቃሴዎችን በማፋጠን የኢኮኖሚውን አቅም ያጎለብታል። የሀገሪቱን ምርቶች በፍጥነት እና በጥራት ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ግዙፍ የሎጀስቲክስ ማዕከል ኾኖም ያገለግላል።
ኢትዮጵያ በራሷ ጥረት የዜጎቿን ሕይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ሜጋ ፕሮጄክቶችን በውጤታማነት እያከናወነች ትገኛለች። የቀጣዩ ትውልድ ብሩህ ተስፋ ዛሬ በምናስቀምጣቸው መሠረቶች እና በምናጠናቅቃቸው ታላላቅ ሥራዎች እየተረጋገጠ ይገኛል።
✍️ በቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ምን ለውጥ አመጣ?
Next articleየአማራ ክልል የዓሣ ምርት አዲስ ተስፋ!