የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ምን ለውጥ አመጣ?

10
🇪🇹
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በመሠረታዊነት የሚቀይር የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። ይህ ሪፎርም መንግሥት ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በሮችን በመክፈት እና የውጭ ምንዛሬ ሥርዓቱን በማሻሻል ረገድ ትላልቅ እርምጃዎችን የወሰደበት ነው።
📌በኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተመዘገቡ ለውጦች ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በቅርብ ጊዜ የተወሰደው የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ማስተካከያ የብር ምንዛሬን ከገበያ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም አድርጎታል።ይህም ጥቁር ገበያን ለማጥበብ እና የውጭ ንግድን ለማበረታታት ያለመ ነው።
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡም የሕግ ማዕቀፎች ተዘርግተዋል። በዚህ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሂደት ላይም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተለያዩ ምልከታዎችን እና ሃሳቦችን ሰንዝረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የወጡ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ይፋዊ መግለጫዎች እንደሚያስረዱትም የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ያስችላል። የኢኮኖሚ መዛባትን ለማስተካከልም ወሳኝ እርምጃ መኾኑን ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (GDP) ዕድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠልም ያግዛል። በኢኮኖሚው ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እና ምርታማነትን ማዕከል ያደረጉ ዘርፎችን ለማጠናከርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል።
ሪፎርሙ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የኢንቨስትመንት ፍሰት ቢፈጥርም የአጭር ጊዜ የዋጋ ግሽበት ጫናው በኅብረተሰቡ ላይ ፈታኝ እንደኾነም መረጃዎች ያመላክታሉ።
በጥቅሉ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ኢኮኖሚውን ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ነው። የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ግን ተጨማሪ የማኅበራዊ ጥበቃ ማዕቀፎች እና የቁጥጥር ሥርዓቶችን ማጠናከርን የሚጠይቅ ይኾናል።
✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ ጌጥ፣ ተናፋቂው ሥፍራ 🇪🇹
Next articleየኢትዮጵያ የአቪዬሽን ከፍታ፤ የቢሾፍቱ ሜጋ ፕሮጄክት እና የኢኮኖሚ አቅም