የኢትዮጵያ ጌጥ፣ ተናፋቂው ሥፍራ 🇪🇹

2

 

ግርማው ከሩቅ ይጣራል፤ ሠንሠለታማ ተራራዎቹ ለእይታ ይማርካሉ። ከተራራው ሥር የሚፈልቀው ቀዝቃዛ አየር ልብን ይሠርቃል። ከተራራው ራስ ኾኖ ታች ያለውን መልክዓ ምድር መመልከት ሀሴትን ይፈጥራል።

ተፈጥሮን ከሙሉ ገጽታዋ ጋር አቅፎ የያዘው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት የሚመጡ ጎብኝዎች በግርማው ደምቀው፣ በውበቱ አብበው፣ በፍካቱ ፈክተው እጃቸውን በአፋቸው ላይ እንደጫኑ ይመለሳሉ።

ተራራዎችን ብቻ ሳይኾን በውስጡ የያዛቸውን ብዝኃ ሕይወትን ተመልክተው ይደመማሉ። በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋሊያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀይ ቀበሮ እና ሌሎች ብርቅዬ እንስሳትን ይመለከታሉ። ሠንሠለታማ ተራራውን፣ ብርቅዬ እንስሳቱን፣ ማራኪ መልክዓ ምድሩን በካሜራቸው ቀርጸው፣ በልባቸው ከትበው፣ በአዕምሯቸው ነድፈው በፍቅር ይሰናበቱታል።

ይህ የተፈጥሮ ቋት ግን ባለፉት ዓመታት ጥቁር ጥላ አጥልቶበት ቆይቷል። በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አስጎብኝ የኾነው ካሳ ብርሃኔ በኮሮና ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ የጸጥታ ችግር ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተጎድቶ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከ2012 ዓ.ም በፊት በዓመት ከ32 ሺህ በላይ ጎብኝዎች የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ይጎበኙ ነበር፤ በተደራራቢ የጸጥታ ችግር ምክንያት ግን በእጅጉ የጎብኝዎች ቁጥር ቀንሶ ቆይቷል ነው ያሉት።

በሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ ካሳሁን ንግሩ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች በስፋት ለመዳረሻነት የሚመርጡት ፓርክ መኾኑን ተናግረዋል።

የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለ ሰላም መራመድ የማይችል በመኾኑ ሁሉም ለሰላም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። ግጭቶችን በውይይት በመፍታት የቱሪዝም ትንሣኤን ማወጅ ይገባልም ብለዋል። የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ፣ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡ የገጽታ ግንባታ ተግባራት እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ እየታየ ያለው ሰላም ለአካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጭ በመኾኑ ጎብኝዎች ወደ ፓርኩ እንዲመጡ በትኩረት ይሠራል ነው ብለዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ፓርኩ የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመገንዘብ የፓርኩን ደኅንነት እየጠበቀ መኾኑንም አንስተዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_30_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ቁርጠኛ መኾኗን የሚያሳዩ ሥራዎች ተሠርተዋል።