ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ቁርጠኛ መኾኗን የሚያሳዩ ሥራዎች ተሠርተዋል።

11
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመተከል፣ ታዳሽ ኀይልን በማልማት እና የአየር ንብረት አደጋዎችን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ በዓለም በታላቅ አርዓያነት የሚጠቀስ ኾኗል። በቱርክ አንታሊያ እየተካሄደ
ካለው የኮፕ-31 መድረክ ጎን ለጎን የተከፈተው የኢትዮጵያ ዐውደ ርዕይ ሀገሪቱ በዘርፉ ያደረገችውን አስደናቂ ጉዞ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታላቅ መድረክ መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ-32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለቀጣዩ የኮፕ-32 ጉባኤ ከፍተኛ
ዝግጅት እያደረገች መኾኗን ጠቁመዋል። ኮፕ ኢትዮጵያ ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ ለማስታረቅ አቅም፣ ዝግጁነት፣ ጉዳዩ የገባት እና በቂ ግንዛቤ ያላት ሀገር መኾኗን የምናሳይበት መድረክ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በኮፕ 32 የድርድር ሂደት የራሷን ጥቅም ብቻ ሳይኾን ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፍትሐዊ እና ጠንካራ ምላሽ የሚሰጥ ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገች ነውም ብለዋል።
የድርድር ድምጿን በማጠናከር ከታዳጊ ሀገራት፣ ከአፍሪካ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ጠንካራ አጋርነቶችን እየፈጠረች ነው። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ቁርጠኛ መኾኗን የሚያሳዩ ሥራዎች ተሠርተዋል። ሚሊዮኖችን በማንቀሳቀስ ቢሊዮን ችግኞችን
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መትከሏ፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚኾነው የኢነርጂ አጠቃቀም ከታዳሽ ኀይል ማግኘቷ፣ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በማበረታታት እና ከተሞችን አረንጓዴ በማድረግ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የሀገሪቱን ተአማኒነት በላቀ ደረጃ አረጋግጠዋል ነው ያሉት።
በዐውደ ርዕዩ የሚከናወኑ ሁነቶች የኢትዮጵያን ብራንድ ከማስተዋወቅ ባለፈ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የሚስቡ፣ የፋይናንስ አጋርነትን የሚያጠናክሩ እና የኢትዮጵያን የቡና ባሕል ጨምሮ ገጽታዋን ለዓለም የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።በአጠቃላይ ዐውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ዓለምን
የሚመራ ተአማኒነት ያለው የአየር ንብረት ፖሊሲ እና የተግባር ሥራዎችን ያካበተች ሀገር መኾኗን በግልጽ የሚያሳይ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በኮፕ 31 በሚኖረን ቆይታ ሰዎች ኮፕ 32ን በጉጉት እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እንሠራለን” ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር)