
በቱርክዬ አንታሊያ መካሄድ በጀመረው የኮፕ 31(COP31) የኢትዮጵያ አውደ ርዕይ ተከፍቷል። በዚህ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በኮፕ 31 ለማሳካት ያሰበቻቸውን ጉዳዮች በተመለከተ
ማብራሪያ ሰጥተዋል። አንደኛው በኮፕ 31 ላይ የሚኖረውን የድርድር ሂደት በኮፕ 32 ላይ ይበልጥ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል መደላድልን መፍጠር ነው ብለዋል። ለዚህም ከቱርክየ እና ከአውስትራልያ ፕሬዝዳንቶች ጋር አብሮ መሥራትን ያለመ እንደኾነ ጠቁመዋል። ሁለተኛው ዓላማ ለኮፕ 32
አጋር የሚኾኑ እና አብረው የሚሠሩ አካላት ጋር መወያየት እና መግባባት መፍጠር መኾኑንም አብራርተዋል። በተጨማሪም “በኮፕ 31 በሚኖረን ቆይታ ሰዎች ኮፕ 32ን በጉጉት እንዲጠብቁ እና ሰፊ ቁጥር ያለው ተሳታፊ በዝግጅቱ እንዲገኝ ማድረግም ሌላው ዓላማችን ነው”
ብለዋል።ከአጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ከፍ በማድረግ ስለ ኢትዮጵያ እንደ ሀገርም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስለምትሠራው ሥራም ዓለም እንዲያውቅ ያግዛል ነው ያሉት። በቆይታቸው በሚደረጉ ውይይቶች እና መድረኮችም ከአሁኑ የኢትዮጵያን አስተናጋጅነት ሰዎች እንዲለማመዱ እና
እንዲናፍቁት ለማድረግ የሚያግዝ መኾኑንም አንስተዋል።ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማዋቀር፣ በማቀድ እና ተሞክሮ በመቀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጀመሯንም ጠቁመዋል። ለዚሁ ተግባር የተቋቋመው ቡድንም በኮፕ 31 ላይ ተገኝቶ ተግባራዊ ሥራዎች እንዴት እንደሚከናወኑ የማየት ዕድል አግኝቷል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
