ባዕድነት የሌለባት፤ ሀሉንም “እህት፣ ወንድም፣ እናት አባት” እያለች የምትጠራ አበቅ የለሽ !

6
የኢትዮጵያ ታሪክ እና ሥልጣኔ ሲነሳ ጎንደር አብራ መነሳቷ ግድ ነው። የኢትዮጵያ የጥንት ኪነ-ሕንጻ ጥበብ አሻራ፤ የድንቅ ባሕል፣ እሴት እና ሃይማኖት መገኛ፤ የጽኑ የሥነ-መንግሥት ምሥረታ ዋና ማዕከል ናት። የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣
የከተማዋ አቀማመጥ፣ የሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት አከባበር፣ የነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነት በእንግዶች ዘንድ የልብ ማኅተሞች ናቸው።
ጎንደርን በአካል የጎበኘ ሁሉ በመደነቅ ስም ያወጣላታል። የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን በ18ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የመጡ የውጭ ሀገር
እንግዶች እና ዲፕሎማቶች በሥልጣኔዋ፣ በኪነ-ሕንጻ ጥበቧ እና ውበቷ ተገርመው “አበቅ የለሽ” ብለዋታል፤ ምንም እንከን የሌለባት ውብ ከተማ እንደማለት። በምዕራባውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ደግሞ በአብያተ መንግሥታቶቿ የግንባታ ጥበብ ተደንቀው “የአፍሪካዋ ካሜሎት” ( መናገሻ)
ሲሏት፤ የሀገር ውስጥ ሊቃውንት ደግሞ “የቅኔ፣ የዜማ እና የባሕል ማማ” ይሏታል። ታዋቂው ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “የሕልሜ ከተማ”
ሲላት፤ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም “እርጅና እና ሙሽርነትን በአንድነት የተጎናፀፈች ድንቅ ከተማ” ብሏታል። በሀገረኛ ዜማዎች የተቀኙላት እና
ያዜሙላት ብዙ ናቸው። ዘመን አይሽሬ ታሪኳ እና ያሏት ድንቅ ቅርሶች ላለፉት በርካታ ዓመታት ጎንደርን የቱሪስቶች ቀዳሚ መዳረሻ አድርገዋት ቆይተዋል። ኾኖም እምቅ የቱሪዝም ሃብቷን ይበልጥ ከማልማት አኳያ የነበሩ ሰፊ ክፍተቶች ሃብቷን ያልተጠቀመች እንድትሰኝ አድርገዋት ነበር።
አሁን ላይ ግን ጎንደር በጥቅሉ ገጽታዋ ከስሟ ጋር ተዋሕዶ አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። በልዩ እሳቤ ተቀርጾ ወደ ትግበራ የገባው የኮሪደር ልማት የጥንታዊነት መልኳ እና የታሪክ ይዘቷን ሳይበርዝ ጎንደርን እንደ አዲስ በመግለጥ እያደር አዲስነቷን አጉልቶታል። የከተማዋን መሠረተ
ልማት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያዘመነው፣ ሰፋፊ እና ጽዱ የእግር ጉዞ መንገዶች፣ ውብ የቱሪስት ማረፊያ አደባባዮች እና መዝናኛ አረንጓዴ ሥፍራዎች የተከናወኑት በዚህ እሳቤ በመኾኑ የኮሪደር ልማት ለጎንደር ተጨማሪ ውበት ኾነዋል። በከተማዋ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ
የተከናወነው የቅርስ እድሳት እና የጥገና ሥራ ደግሞ የዘርፉ ትልቁ ስኬት ኾኗል። በተለይም የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች ጥንታዊነታቸውን ጠብቀው ታድሰዋል። እነዚህ የቱሪስት ፍሰቷን እያነቃቃው እንደሚገኝም ነዋሪዎቿ ምስክር ናቸው። ጎንደር ከታሪኳ እና
ከቅርሶቿ ባሻገር የነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነት የቱሪዝም ስኬቷ ምልዑነት ትልቁ ምሰሶ ኾኖ ቀጥሏል። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይሸራረፍ
የተሻገረው የከተማዋ ነዋሪዎች መልካም ሥነ-ምግባር፣ ለእንግዳ የሚሰጠው ክብር እና ፍቅር የኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት መገለጫ
መስታወት ነው። የጎንደር ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነት ባዕድነት ፈጽሞ የሌለበት ነው። ሰውን ለመጥራት መጠሪያ ስምን ማወቅ ሳይገድ እንደዬ ዕድሜው እህት፣ ወንድም፣ እናት፣ አባት የማንኛውም የሰው ልጅ የወል መጠሪያ ነው። በጎንደር እያንዳንዱ ከተማዋን የሚረግጥ ጎብኝ ከሕጻን
እስከ አዋቂ ሞቅ ያለ አቀባበል እና እንክብካቤ ይደረግለታል። ይህም ማንኛውም ሰው ጎንደርን ማየት የሕይወት ዘመን ትልቁ ምኞቱእንዲያደርጋት የሚገፋፋ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። ይህ ልዩ የነዋሪዎች ባሕል የቱሪዝም ፍሰቱን አሳድጎታል። ጎብኝዎች የኢትዮጵያን ትክክለኛ ታሪክእና ማንነት
ይበልጥ እንዲወዱ በማድረግ ረገድም የላቀ ሚና ይጫወታል። በጥቅሉ አዲሱ የከተማ ልማት ውጤት እና የሕዝቡ የቆዬ መልካም እሴት ተደማምረው የጎንደርን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነት እና የቱሪዝም ዘርፍ ቀዳሚነትን እያስቀጠሉ ይገኛሉ።
✍️በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየቱሪስቶችን ዓይን የሚስበው ታላቁ የተፈጥሮ ጸጋ፤ ጭስ ዓባይ ፏፏቴ
Next article“በኮፕ 31 በሚኖረን ቆይታ ሰዎች ኮፕ 32ን በጉጉት እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እንሠራለን” ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር)