
ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል አንዱ ነው፤ የቱሪስቶችን ዓይን ይስባል፤ መንፈስን ያድሳል፤ የደስታ ሀሴትንም ይፈጥራል። ተፈጥሮ ውበትን ሳይሰስት ያደለው፤ ሕያው የውበት ማኅደር የኾነው እና ከጣና በአሻገር የሚፈነጥቀው ድንቅ ተፈጥሮ ጭስ ዓባይ ፏፏቴ።
ፏፏቴው በሸለቆዎች መካከል የሚታይ እና ሰፊውን አረንጓዴ ምድር አስተሳስሮ፣ ነጭ ለብሶ የሚፈስስ ነው። የውኃው ዥረት ወደ ታች ሲወርድ ለእይታ ማራኪ የኾነ ቀስተ ደመና ይፈጥራል። የጭስ ዓባይ እና አካባቢው አስጎብኝ ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ይበልጣል አደገ ጭስ ዓባይ ፏፏቴ
ከባሕር ዳር ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ብለዋል። በፏፏቴው አካባቢ ነጭ ጉም የለበሰው ሰማይ በቀስተ ደመና ተሸልሞ ይታያል ነው ያሉት። ውኃው ከላይ ወደ ታች ሲወርድ የሚፈጥረው ነጎድጓዳማ ድምፅ እንደ አንበሳ የሚያገሳ ድባብ እና
የኢንዱስትሪ መንደር ያስመስለዋል ይላሉ። ትልቅ መንፈስን የሚያድስ የተለየ ሀብት መኾኑን የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ አካባቢውን ለማስተዋወቅ ለእንግዶች አምባሳደር በመኾን እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ፏፏቴው ዓመቱን ሙሉ የሚጎበኝ ድንቅ ሀብት ነውም ብለዋል። ወደ ሥፍራው ለመጓዝ ከጭስ ዓባይ ከተማ ሁለት አማራጮችን መጠቀም ይቻላል። የመጀመሪያው አማራጭ ከከተማው ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በእግር
በመጓዝ፣ የዓባይን ወንዝ በጀልባ በመሻገር ወደ ፏፏቴው የሚያደርስ ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከከተማዋ በተሽከርካሪ ከተጓዙ በኋላ ጥንታዊውን የዓባይ ድልድይ በመሻገር በእግር ወደ ፏፏቴው ያደርሳል። በአካባቢው በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት የተገነባው የዓባይ ወይም
የእንቁላል ድልድይ ደግሞ ሌላ ውበትን ደርቦለታል ነው ያሉት። በአካባቢው የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የተደራጁ ወጣቶች መኖራቸውን የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል እያስተናገዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የባሕር ዳር ከተማ
አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አትርሳው ዓለም የጭስ ዓባይ ፏፏቴ 400 ሜትር ስፋት እና 45 ሜትር ጥልቀት ያለው እጅግ ድንቅ እና ገራሚ ተፈጥሮ መኾኑን ገልጸዋል። ከፏፏቴው የሚወጣው ጭስ እና የሚረጨው እርጥበት አዘል
ጉም የተፈጥሮን ድንቅነት በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል። ሀብቱን ጥበቃ ከማድረግ ባለፈ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል። መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ ዓለም አቀፋዊነቱን ለማጉላት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
