
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ቀዳሚ ምሽግ በመኾን እና የሉዓላዊነት ምልክት ኾና በመዝለቅ ከዘመናዊው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥርዓት ጋር በጥልቀት የተሳሰረች፣ ታሪካዊ እና አኩሪ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ማዕከልነት ያላት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በአውሮፓ የቅኝ ግዛት ማዕበል መሐል ነፃነቷን በጽናት በማስከበር ለዓለም አቀፍ ሕግ እና ለጋራ ደኅንነት የነበራትን ቁርጠኝነት አሳይታለች። እ.አ.አ በ1923 የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል መኾኗ እና በኋላም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲሸጋገር ከቀዳሚዎቹ መሥራች አባላት አንዷ ኾና አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ድምጽ እንዲኖራት አድርጋለች። የዓድዋ ድል እና የሕዝቦች እኩልነት መርሆ የኢትዮጵያን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የነፃነት፣ የኩራት እና የአንድነት ተምሳሌትነት በሰፊው ያጸኑ አበይት ምሰሶዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትን መሠረት በመጣል እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) ዋና መሥሪያ ቤቶች መገኛ በመኾኗ አዲስ አበባ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ መዲና ኾናለች። ይህም ሀገሪቱ እ.አ.አ ከ1963 ጀምሮ የአፍሪካ መሪዎች የሚሠበሠቡበት፣ የሰላም ስምምነቶች የሚፈረሙበት እና የጋራ አቋሞች የሚቀረጹበት ማዕከል እንድትኾን በማድረግ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳረጋገጡት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መርህ በሦሥት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ የተመሠረተ ነው። ከዘመን ዘመን የማይቀየረው የነፃነት፣ የእኩልነት እና የፍትሐዊነት መርህን ቀዳሚ በማድረግ ጠቁመዋል።የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካ መፍትሔ ማግኘት አለባቸው የሚለው የፀና አቋም እና አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚኾንበትን አካሄድ በማስቀረት በጋራ የሚያሸንፍ አቀራረብን መከተል የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርሆዎች ናቸው። እነዚህ ሁሉ አካሄዶች የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲጉዞ ስኬታማ አድርገውታል። ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በአየር ንብረት ለውጥ ለአፍሪካ ድምጽ በመኾን ዛሬም ግንባር ቀደም ናት። የብሪክስ ኅብረት አባልነቷም ጂኦስትራቴጂያዊ ሚዛኗን ከማሳደጉም በላይ በዓለም አቀፍ መድረኮችተወዳዳሪነቷን እና ተአማኒነቷን እያጎለበተ ይገኛል። የኢትዮጵያን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ከፍታ እና ማዕከልነት በማስቀጠል አሁን ባለው የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር ውስጥ የባሕር በር ባለቤት የመኾን መብትን ጨምሮ ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ልማትን ማረጋገጥ የዘመኑ ትውልድ ኀላፊነት ሊኾን ይገባል።
#EthiopianDiplomacy #Sovereignty#PanAfricanism#አሚኮ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
