
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእምነት፣ የጽናት፣ የታሪክ እና የድንቅ ጥበብ ትስስር ማሳያዎች ናቸው። ከላይ ወደ ታች በመንደፍ ከአለት ተፈልፍለው የታነጹት እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ ያቆማቸው መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ሀብቶች ናቸው። የኢትዮጵያን የሕንጻ ጥበብ ምጥቀት የሚያሳዩት እነዚህ ቅርሶች በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኾነው መመዝገባቸው ይታወቃል። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት
የኢትዮጵያን ጥንታዊ የምህንድስ ጥበብ እና ጥልቅ ሃይማኖታዊ ጸጋ አጣምረው የያዙ የጥበብ መኩሪያዎች ናቸው። ታዲያ ከአለት የተፈለፈሉት እነዚህ ድንቅ የጥበብ ሥራዎች በየዓመቱ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በመሳብ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በየዓመቱ በሚከበረው ታኅሣሥ 29 ክብረ በዓል ቀን ቁጥራቸው የበዛ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ
ስፍራው ይተምማሉ። በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢም ይሠበሠባል። በቅርብ ዓመታት በነበሩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የክልሉ የጸጥታ ሁኔታዎች ምክንያት የጎብኝዎች ቁጥር መለዋወጥ አሳይቶ የነበረ ቢኾንም በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም እና የንግድ እንቅስቃሴው ወደነበረበት የመመለስ እና የማያንሠራራት ሂደት ላይ ይገኛል። ላሊበላ እነዚህን ቅርሶች ለመጎብኘት ወደ ሥፍራው የሚመጡ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን እንደ
ትላንቱ ሁሉ ዛሬም በፍቅር እና በክብር ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መኾኗን አብስራለች። የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶችን ማስተናገድ የዘመናት ባሕላቸው እና መለያቸው በመኾኑ የሚመጡ ጎብኝዎችን በሞቅታ እና በጨዋነት ለመቀበል ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። በላሊበላ
እና አካባቢው ሰላም ሰፍኗል። የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘርግቷል፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እናሬስቶራንቶችም እንግዶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር እንዳስታወቀው ባለፈው ዓመት በሺህዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር
ጎብኘዎችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ላሊበላን ጎብኝተዋል። ዘንድሮም የተሻለ የጎብኝዎች ቁጥር ለማስተናገድ እና የተሻለ ገቢ ለማስመዝገብ አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ እና የጎብኝዎችን ጊዜ ለማራዘም የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል። “ላሊበላ እንደገና
የዓለምን ትኩረት ለመሳብ ተዘጋጅታለች” የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የዓለም አቀፍ ጎብኝዎች የሰው ልጅ የእጅ ጥበብ ውጤት እና የመንፈሳዊነት ድንቅ መገለጫ የኾነችውን ታሪካዊቷን እና መንፈሳዊቷን ላሊበላን እንድትጎበኙ ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
