
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በባሕል እሴቶች የበለጸጉ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ያሏት ሀገር ናት። የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ከታሪክ ተመራማሪዎች እስከ ተፈጥሮ አድናቂዎች፣ ከሃይማኖት ተጓዦች እስከ ባሕል አጥኝዎች፣ ከግለሰብ እስከ መንግሥታዊ ስብሰባዎች ለሁሉም
የሚመች አያሌ አማራጮችን የያዘ ነው። ከውርጭ እስከ በረሀ የሚያካልል ሥነ ምኅዳር፣ ከራስ ደጀን እስከ ዳሎል የሚዘልቅ አስደናቂ መልከዓምድር የሀገሪቱን የብዝኀ ቱሪዝም ጸጋን በግልጽ ያሳያል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል
ድርጅት(UNESCO) በርካታ ቅርሶችን ያስመዘገበች ግንባር ቀደም አፍሪካዊት ሀገር ናት። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሐረር ጀጎል
ግንብ፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የአክሱም ሐውልት፣ የሶፍ ዑመር ዋሻዎች እና ሌሎች በአብነት የሚጠቀሱ የባሕል እና የታሪክ ሀብቶቿ
ናቸው። ከ6ሺህ በላይ ለሚኾኑ የዕፅዋት ዝርያዎች፤ እንደ ዋሊያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ቀይ ቀበሮ ያሉ ብርቅየ እንስሳት ባለቤት መኾኗ በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ የአድቬንቸር ቱሪዝምን ለሚመርጡ ጎብኝዎቿ ተመራጭ ያደርጋታል። ከቤተ መንግሥቱ የጀመረው የቅርስ ጥገና፣ ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለትውልድ የተገነቡት አዳዲስ ፕሮጄክቶችም የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክ የገለጡ፣ ጸጋዋን ለዓለም ያሳዩ ኾነዋል።
የዓለም የጎብኝዎች ዐይን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያማትሩም ያማለሉ መዳረሻዎች ኾነዋል። ዘመናዊነትን እና ከተሜነትን አዋህዶ ለኢትዮጵያ ከተሞች ሕዳሴን ባበሰረው የኮሪደር ልማትም አዲስ አበባን ከታላላቆቹ የዓለም ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ አድርጓል፣ ለጎብኝዎችም ማራኪ የስበት ማዕከልነትን ፈጥሯል። በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞቿ የተገነቡት ግዙፍ የመሠብሠቢያ ማዕከሎቿ፣ ዘመናዊ ሆቴሎቿ፣ የዲጂታል መሠረተ
ልማት ሥርዓቶቿ ለዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንሶች መዳረሻ እንድትኾንም አስችሏታል። በአየር ትራንስፖርት ዘርፉም የሀገር ውስጥ የመዳረሻ ቁጥርን
አሳድጋለች። እንግዶች ከቦታ ቦታ በምቾት የሚንቀሳቀሱባቸው በርካታ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን አስፋፍታለች። እነዚህ ጸጋዎች ተደምረው
ኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የጎብኝዎች መዳረሻ አድርገዋታል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2018 በጀት
ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የዓለም አቀፍ እና ከ50 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን አስተናግዳለች። በዚህም ከዓለም
አቀፍ ጎብኝዎች 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር፣ ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ደግሞ ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝታለች። 204 የዓለም አቀፍ
ጉባኤዎችንም በስኬት ማስተናገድ ችላለች። 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32)ን በስኬት
ለማስተናገድም ተዘጋጅታለች። በ32ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የሚሳተፉ የዓለም መሪዎች እና ተሳታፊዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ
ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ቅርስን፣ ባሕልን፣ ጥበብን እና ዘመናዊነትን በአንዲት ሀገር በእያንዳንዱ መዳረሻ በአይነት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትን ሰንዳ፣ ታሪክን ከዛሬ አዋህዳ፣ ዛሬን ከነገ አስተሳስራ በአረንጓዴ የልማት ተስፋ የምትቀጥል ድንቅ ሀገር ኾና ዘመናትን ትሻገራለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
