የሠራባ መስኖ ፕሮጄክት የአርሶ አደሮችን ሕይወት እየለወጠ ነው።

7
በአማራ ክልል ከሚገኙ ስትራቴጂካዊ የመስኖ ፕሮጄክቶች መካከል የሠራባ መስኖ ፕሮጄክት አንዱ ነው። ፕሮጄክቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የምሥራቅ እና ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አርሶ አደሮችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በዘላቂነት እየቀየረ ይገኛል። በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ
የጉራምባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መልካሙ ነጋሽ የመስኖ ፕሮጄክቱ ከሚያገኙት የሰብል ምርት ባሻገር፣ ለእንስሳት ውኃ መጠጥ፣ ለንብ እርባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጸውልናል። አሁን ላይም አንድ ሄክታር መሬታቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት መዘጋጀታቸውን
አስገንዝበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከ400 በላይ የሚኾኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ስንዴን በኩታ ገጠም ለማልማት ማሳቸውን በማረስ እና በማለስለስ ላይ ይገኛሉ። በዚሁ ወረዳ የሠራባ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ሌላኛው አርሶ አደር አወቀ ሽፈራው ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ ልማት
ሥራዎች በመሳተፍ የምርት ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለዚህ ዓመታዊ የልማት ምዕራፍም ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት አስፈላጊውን የማረስ እና የማለስለስ ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሤ ማለደ
የሠራባ መስኖ ፕሮጄክት ከ4 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም አለው ብለዋል። የሠራባ መስኖ ፕሮጄክት የበጋ መስኖ ልማት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት። የመስኖ ካናሉ አምስት በመብራት የሚሠሩ ፓምፖች
ይኑሩት እንጅ እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ሁለቱ ብቻ መኾናቸው በአርሶ አደሮች ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄ ኾኖ ቆይቷል ብለዋል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሦስቱን የውኃ መሳቢያ ፓምፖች በአዲስ ማሽን በመተካት ወደ ሙሉ አቅም ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው
ነው ያሉት። ፕሮጄክቱ እነዚህን መሰናክሎች አልፎ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ2 ሺህ 800 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም የነበረውን የመብራት ኢንስታሌሽን ችግር አሁን ላይ መስተካከሉን ያነሱት ኀላፊው ትልቁን ካናል
በየጊዜው በኤክስካቫተር በማጽዳት እና ትንንሾቹን ካናሎች ደግሞ በአርሶ አደሮች አቅም በማጽዳት ለልማት እየዋሉ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህ ዓመት ስንዴን በኩታገጠም ለማልማት አሁን ላይ አርሶ አደሮች የማለስለስ እና ዘር የመዝራት ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ለዚህ ስኬትም ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መኾኑ ተጠቁሟል።
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article🐝 “በአማራ ክልል 40 ሺህ ቶን የማር ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ ነው”
Next articleኢትዮጵያ ከመላው ዓለም ለሚመጡ እንግዶቿ የምትገልጠው ድንቅ ማንነት!