
አርሶ አደር ወርቅነህ ጋሼ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ ከግብርና ሥራቸው ጎን ለጎን በንብ ሀብት ልማት ተሠማርተው ኑሯቸውን እየመሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ባሕላዊ፣ ዘመናዊ እና የሽግግር ቀፎዎችን በመጠቀምም በዓመት እስከ 150 ኪሎ ግራም የማር ምርት እንደሚያመርቱ ተናግረዋል።
በዘርፉ በመሠማራት ከችግር ተላቅቀው የራሳቸውን ኑሮ መምራት መቻላቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ የተሰጣቸውን የባለሙያ ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የንብ ሀብት ልማት የማር ምርት የኑሮዬ መሠረት ነው የሚሉት አርሶ አደሩ የተሻሻሉ አሠራሮችን በመከተል ዘንድሮ ከ250 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት እንደሚጠብቁ አንስተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ትዛዙ አበበ በንብ ሀብት ልማት ዘርፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ኅብረ ንብ የማባዛት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የችሎታ ማሳደጊያ ሥራዎችን በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 4 ሺህ 232 ቶን የማር ምርት ለማምረት ታቅዶ እስካሁንም 639 ቶን ማር መሠብሠብ መቻሉን ገልጸዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የቀሰም እፅዋትን እንዲያለሙ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል። የማር ምርታቸውን በጥራት በማምረት ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ መደረጉንም አንስተዋል። የማኅብረሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ የንብ ሀብት ልማት ባለሙያ መሐመድ ጌታሁን እንደ ክልል በበጀት ዓመቱ 40 ሺህ ቶን የማር ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ኅብረ ንብ ይገኛል ያሉት ባለሙያው በዘርፉ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በባሕላዊ፣ በሽግግር እና በዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በመጠቀም የማር ምርቱን በስፋት እያመረቱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ሀብት የሚገኘውን የማር ምርት ለማሳደግ ከባሕላዊ ወደ ዘመናዊ አሠራር የመቀየር እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመተግበር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
የማር ምርት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሠበሠብ እንደኮነም ተናግረዋል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 14 ሺህ ቶን የማር ምርት መሠብሠቡን ነው ያስረዱት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_30_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
