
አዲስ አበባ በሚገኘው ታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከጥቅምት 26/2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም ሲካሄድ የሰነበተው 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ (APPS 2026) በታላቅ ስኬት ተጠናቅቋል።
ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የገዢ እና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና የፓርላማ አባላት ተሳትፈውበታል። ይህ ጉባኤ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ተቀባይነት እና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት እጅግ ከፍተኛ ትርጉም አለው።
ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀባይነት ካበረከታቸው መካከልም የአህጉራዊ ፖለቲካ መሪነትን በእጅ ማስገቢያ አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላይ እንዳገኘነው መረጃ ኢትዮጵያ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ አዲሱን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ በሊቀመንበርነት እና በዋና ጸሐፊነት እንድትመራ በሙሉ ድምጽ ተመርጣለች። ይህም የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል። ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫዎች የመቅረጽ አቅም እንዳላት ማረጋገጫም ነው።
የጉባኤው ተሳታፊዎች የአፍሪካን የወደፊት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ተቋማዊ ትስስር እና የኢኮኖሚ ሽግግር የሚመራ ባለ 22 ነጥብ ታሪካዊ “የአዲስ አበባ ድንጋጌ (Addis Ababa Declaration)” አጽድቀዋል።
ይህ ሰነድ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ስም ተሰይሞ መውጣቱ በራሱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አሻራ በአፍሪካ ታሪክ ማኅደር ውስጥ በጉልህ ያስቀምጠዋል። ይህም አንዱ የተገኘ ውጤት ነው።
በ2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ መክፈቻ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቀረበው የ”መደመር” እሳቤም በአህጉሪቱ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት እና ተቀባይነትን አትርፏል። ይህም ሌላኛው የተገኘ ውጤት ነው።
አፍሪካ ላይ ያሉ መከፋፈሎችን በማሸነፍ ለዘላቂ ሰላም እና ለአህጉራዊ ትስስር ይህ ፍልስፍና እንደ ትልቅ መፍትሄ መወሰዱ የሀገሪቱን የፖለቲካ ትረካ ከሀገር ውስጥ አልፎ አህጉራዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎታል።
ሌላው የሀገር ውስጥ የሪፎርም ፖሊሲዎች በአርዓያነት መወሰዳቸው ነው። የጉባኤው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን (የኮሪደር ልማትን ጨምሮ) እና የተመዘገቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬቶችን በተግባር ተመልክተዋል። ይህ ተሞክሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተላቸው የልማት እና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ለአፍሪካ ሀገራት በተምሳሌትነት እንዲጠቀሱ በማድረግ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቿን ተዓማኒነት ከፍ አድርጎታል።
ጉባኤው የዲፕሎማሲ ማዕከልነትን እና የፓን አፍሪካኒዝም እምብርትነትን የማደስ አንድምታም አለው። በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱም መላው አፍሪካውያን የጋራ የነጻነት ታሪካቸውን እንዲያስታውሱ ያደርጋል። ከዛ ባሻገርም ኢትዮጵያ አሁንም ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ያላትን ቁርጠኝነት አስመስክሯል።
ኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ትልቅ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ መቻሏ ሀገሪቱ ያላትን አስተማማኝ ሰላም እና የዲፕሎማሲያዊ መድረክነት ብቃት በተግባር ያሳየ ነው።
በጥቅሉ ከተለያዩ የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚያመላክቱት 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ጉዳዮች ላይ ያላትን የነቃ የሰላም እና የልማት አጋርነት የሚያሳይ ነው። የፖለቲካ ተቀባይነቷን እና ዲፕሎማሲያዊ መሪነቷንም ዳግም ያረጋገጠችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ኾኖም አልፏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
