
የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ላስተዋለ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍን እና አይበገሬነቷን በጉልህ ያገኛል። ገጾቿን ሲገልጥ በየወቅቱ የሚፈጠሩ መሰናክሎችን በጽናት በማለፍ ሉዓላዊነቷን ማስጠበቋ የኩራት ምንጭ እና የቀጣይነት ዋስትናዋ ኾኖ ያገኘዋል።
በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት የተዳከመ ሲመስላቸው ታሪካዊ ጠላቶቿ የውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴዋን በማወክ ዓላማቸውን ለማሳካት ሢሠሩ ቆይተዋል።
ኾኖም ከውስጥ የፖለቲካ ትኩሳቶች እና ከውጪ የሚመነጩ ጫናዎችን፣ ተደጋጋሚ ሴራዎችን በማክሸፏ ኢትዮጵያ ዘመናትን በድል መሻገሯን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ጠላቶቿ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲወድቅ፣ ኢትዮጵያ የሚገባትን ልማት እንዳታለማ ለማድረግ የውስጥ ታጣቂዎችን ሲደግፉ እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር በየወቅቱ ሲሞክሩ ይስተዋላል።
ጠላቶቿ ኢትዮጵያን ከውስጥ ለማፍረስ እና ለማዳከም ሠርተዋል፤ እየሠሩም ይገኛሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በውስጥ ጉዳዮቿ ጣልቃ በመግባት፣ የውኃ ሃብቷን እንዳትጠቀም ተጽዕኖ በመፍጠር እና ለውስጥ ባንዳ ታጣቂዎች የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ በግልጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠሩ ነው።
ተደጋጋሚ ሙከራቸው የከሸፈባቸው ጠላቶቿ የኢትዮጵያ አቅም ካሰቡት እና ካቀዱት በላይ ኾኖባቸዋል። ፈተናዎች የማይበግሯት ኢትዮጵያ ከታሪክ ባገኘችው ጽናት፣ አይበገሬነት እና ጀግንነት ጠላቶቿን አንበርክካለች።
የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ፣ የባዕዳን ተላላኪ የውስጥ ባንዳዎችን በመቅጣት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን በማረጋገጥ በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን አስቀጥላለች።
ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂዎችን ከብቁ ወታደራዊ ኀይል ጋር በማጣመር ከሀገሪቱ አልፎ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላም እና ደኅንነት አለኝታ እየኾነች ነው። በቅርቡ ከሩሲያ የገዛቻቸው የጦር ቴክኖሎጂዎችም ለቀጣናው ሰላም በጽናት እየሠራች መኾኑን ማሳያ ናቸው። በቀጣናው ጠንካራ አቅምን በመገንባት ጠላቶቿን አንገት አስደፍታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ለውስጥ ለታጣቂዎች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን አይችሏትም ብለዋል። ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ለዘመናት በጽናት ማለፏንም ተናግረዋል።
ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን አትንኩ፣ ኢትዮጵያን አትሞክሩ አታሸንፏትም ብለዋል። ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጅ መሸነፍ አያውቅም ነው ያሉት። ሰላምን ማጽናት እንፈልጋለን ደፍሮ የሚሞክረን ካለ ግን ግብዓተ መሬቱን እናፋጥናለንም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
