
ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል ያጋጠመው ግጭት ሕዝቡን ለበርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች ዳርጓል። ሰው በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ፣ ሃብት እንዲወድም፣ ልማት እንዲቀዛቀዝ፣ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ኾኗል።
ግጭቱ በሁለት ተዋጊ ኃይሎች ብቻ የተወሰነ ሳይኾን የእያንዳንዱን ቤት ያንኳኳ ኾኗል። የበርካቶችን ሕይወት አጨልሟል፣ ኑሮን አመሰቃቅሏል። በርካታ ሕጻናት ያለ አሳዳጊ፣ አረጋውያንን ያለ ጧሪ ቀባሪ አስቀርቷል። እናቶችንም የወላድ መካን አድርጓል።
ማኅበረሰቡም የቀደመው ሰላም እንዲመለስለት ዛሬም “የሰላም አየር ይንፈስ ሰላም ይሁን አድባሩ፤ ሕዝቡም እፎይ ይበል አይሳቀቅ በመንደሩ።” በሚል አሰተሳሰብ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ አጥብቆ ይሻል።
መንግሥትም ውይይቶችን እና ምክክሮችን መሠረት ያደረገ የሰላም አማራጮችን መዘርጋቱ ይታወሳል። ይህንን ተጠቅመው በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ ወደ ማኅበረሰቡ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
እነዚህ ታጣቂዎች በተሳሳተ መንገድ ገብተውበት ከነበረው የጫካ ትግል ወደ ሰላም አማራጭ በመመለሳቸው የራሳቸውን ሕይወትም አትርፈዋል። ክልሉን እና ማኅበረሰቡንም ከተጨማሪ ጉዳት ታድገዋል።
በክልሉ የተለያየ አካባቢዎች ወደ ሰላም የተመለሱት ታጣቂዎች እንደሚናገሩት በጫካ ትግል ከእርስ በርስ መተላለቅ ውጭ ምንም ጥቅም እንደሌለው ያነሳሉ። በግጭቱ ማኅበረሰቡን እና ክልሉን በሁለንተናዊ መልኩ እየጎዳው እንደኾነም ይገልጻሉ።
ለአብነትም በማዕከላዊ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ወደ ሰላም የተመለሱ ታጣቂዎች እንደተናገሩት “በጫካ ትግል መቆየታችን ተጸጽተናል፤ አሁን ደስ ብሎን የሰላም አማራጭን ተቀብለን ተመልሰናል” በማለት ታጣቂዎቹ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል።
“ሕዝቡን ለጉዳት ዳርገነዋል፤ ለበደልነው ሕዝብም ለመካስ ወስነናል” የሚሉት ታጣቂዎቹ ሌሎች በጫካ የቀሩ ታጣቂዎችም “ግጭቱ የወንድማማቾች የእርስ በርስ እልቂ” መኾኑን በመገንዘብ የሰላም አማራጭን ተቀብለው እንዲገቡ መክረዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸው ለሌሎቹም መንገድ የሚከፍት ነው። ይህም ለዘላቂ ሰላም መስፈን እና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ የመፍታት አማራጭን የሚያጎለብት ነው።
ሕዝቡም እፎይ እንዲል፣ በቀየው እና በመንደሩ ደህንነት እንዲሰማው፣ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ፣ ልማት እንዲመጣ አስተማማኝ ሰላም ወሳኝ ነው። ቅድሚያ ለሰላም እጅ በመስጠት አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ለሁሉም ዋስትና የሚኾን ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አሁን ያለውን ሰላም ማጠናከር፣ የጸጥታ ኃይሉን የበለጠ ማገዝ እና በቁርጠኝነት መሥራት የ2019 በጀት ዓመት ዋነኛ ተግባር መኾኑን መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
