የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት እና ታሪካዊ እውነታ

5
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር መራቋ በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ታሪካዊ ስብራት ነው። ብዙዎች የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ትስስር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የቀደመው የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ወይም ውህደት ያስገኘው እንደኾነ አድርገው ሊስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን እውነታው ከዚህ እጅግ የራቀ እና ጥልቅ ነው።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ቁርኝት ትናንት የተጀመረ ሳይኾን ከጥንታዊው የአክሱም ስልጣኔ ዘመን ጀምሮ የነበረ የታሪክ፣ የምጣኔ ሀብት እና የጂኦፖለቲካዊ ህልውና መሰረት ነው።
ጥንታዊቷ የአዱሊስ ወደብ በዓለምአቀፍ የንግድ መስመር ላይ የነበራት ሚና ኢትዮጵያን ከግሪክ፣ ሮም፣ ህንድ እና ከሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ጋር ያገናኘ የባሕር በር እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል።
ባለፉት ቀደምት ዘመናት የአሰብ እና ምጽዋ ወደቦች የኢትዮጵያ የባሕር ንግድ፣ የወታደራዊ ኀይል ማዘዣ፣ የሥልጣኔ እና ባሕላዊ ትስስር ማዕከል ኾነው ዘልቀዋል።
በመሆኑም ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የቀደመ ክብሯ፣ የኢኮኖሚ ብልጽግናዋ እና የጂኦፖለቲካዊ ገናናነቷ ዋና አምድ የነበረ እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በስጦታ የተገኘ እንዳልኾነ ታሪክ ምስክር ነው።
በሀገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ በውስጥ እና በውጭ ተንኮል እንዲሁም በሴራ የተቀናጀ አካሄድ ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር እንድታጣ እና የቀደመው ጠንካራ የባሕር ኀይሏ እንዲፈርስ ተደረገ። ይህ ውሳኔ ሀገሪቱን በቀጥታ የባሕር በር አልባ በማድረግ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ተግዳሮት ውስጥ ጥሏታል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ በሴራ እና በተንኮል የባሕር ኀይላችን እንዲፈርስ ብሎም የባሕር በር እንድናጣ መደረጉም ሀገራችንን ለተለያዩ ተግዳሮቶች መዳረጉን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊ ስብራት ለመጠገን እና የሚገባትን የተፈጥሮ እና የታሪክ መብቷን ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሌላ ሀገርን ለመውረር ያለመ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ሕግና በዲፕሎማሲ አማካኝነት መፍትሔ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መኾኑንም ዋና አዛዡ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተበተነውን እና የፈረሰውን የባሕር ኀይል እንደ አዲስ በማደራጀት፣ የሰው ኀይልን በማሰልጠን እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት ሂደት ላይ ትገኛለች።
#AMECO ​#የባሕር በር#ታሪክ#አዱሊስ#Ethiopia
አሚኮ-ጥቅምት_29_2019_ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ከሰው ጥበብ የረቀቀች፣ ከምድር ዕውቀት የተለየች”