
በዚያች ምድር ከሰው ጥበብ የረቀቀች፣ ከምድር ዕውቀት የተለየች፣ ሰማይን በምድር የገለጠች፣ መጽሐፍን በዓለት ላይ የቀረጸች፣ ሃይማኖትን በድንጋይ ላይ የጻፈች፣ ታሪክን በአለት ላይ ያተመች ረቀቂ ሥራ አለች።
በዚያች ምድር የሚታያውን ዓለም ጥበብ የናቀች፣ ከሰዋዊ ጥበብ ሁሉ የበለጠች፣ ፈጽማ የጀመረች፣ ጣሪያ ሠርታ መሠረት ያቆመች፤ ከተለዩት የተለየች ድንቅ ሥራ ትገኛለች።
በዚያች ምድር የነገሡ ነገሥታት ካህናት ናቸው በቤተ መቅደስ ይቀድሳሉ፤ በአውደ ምኅረት ይባርካሉ፤ ነገሥታት ናቸው በዙፋን ላይ ተቀምጠው የተስተካከለውን ፍርድ ይሰጣሉ፤ መልካሙን ነገር ለተወደደ ሕዝባቸው፣ ለተመረጠች ሀገራቸው ያደርጋሉ፤ ክህነታቸው ንግሥናቸውን አልከለለውም፤ ንግሥናቸውም ክህነታቸውን አልጋረደውም፤ ይልቅስ ንጉሥ ወ ቅዱስ ኾነው ኖሩ እንጂ። እንዲህ ኾነው የኖሩባት ያቺም ሥፍራ ቅድስቲቷ ሮሃ ናት።
በዚህች ምድር ንግሥናን ከቅድስና፣ ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት አመቻችተው ከኖሩት ነገሥታት መካከል ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ አንደኛው ናቸው። እርሳቸው እንደ ንጉሥ ያማረ ቤተ መንግሥት አልሠሩም፤ ለእግራቸው መጫሚያምም በወርቅ የተበጀ ጫማ አላሠሩም፤ ይልቅስ በድንኳን እየኖሩ ዘመን የማያደበዝዛቸውን፣ ታሪክ እጹብ ድንቅ ብሎ የመዘገባቸውን፤ በሠርክ ሰው ሁሉ የሚደነቅባቸውን፣ አይቶ የማይጠግባቸውን፣ ጀሮ ስለ እነርሱ ለመስማት የሚያዘነብልባቸውን፣ እግርም ይመላለስባቸው ዘንድ ወደ እነርሱ የሚያመራባቸውን፣ ትውልድ ሁሉ የሚኮራባቸውን፣ የሚመካባቸውን፣ ምድሯም የጠቢባን ምድር መኾኗን የሚያሳይባቸውን አብያተ ክርስቲያናትን ሠሩ እንጂ።
በዚያች ምድር አለት እንደ ግራምጣ ተሰንጥቋል፤ ጥበባዊነት፣ መንፈሳዊነት እንደ ዥረት ሲፈስስ ታይቷል። ሮሃ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን ሰማይ ትመስላለች፤ በሰማይ ያለውንም በምድር ትገልጣለች።
በገድለ ቅዱስ ላሊበላ እንዲህ ተጽፏል አብያተ ክርስቲያናቱ ግሩም እና ድንቅ ናቸው። ተወዳዳሪም የላቸውም። በዓለምም ተመሳሳይ አልተገኘላቸውም።
የእነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ሥራ መናገር በምን አንደበት እንችላለን? የውስጣቸውንስ እንተውና የቅጽራቸውን ሥራ እንኳ መናገር አንችልም። ያየም በማየት አይጠግብም፤ ልቡ ዐርፎ ከማድነቅ ቸል አይልም። በላሊበላ እጅ የተሠሩትን አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻ ሥራ ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣ ባይኖቹም ይይ ተብሎ ተጽፏል።
ላሊበላ ከአንድ አለት ድንጋይ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ሲሠሩ ለግድግዳቸው እንጨት፣ ለመሠረታቸውም ጭቃ፣ ለጣራቸውም ባጥ፣ እንጨት እና የገመድ ትት፣ ለክዳናቸውም የሰንበሌጥ ሣር የላቸውም ተብሎ ተመዝግቧል።
ሊቀ ትጉሃን ጌጡ ዘለቀ ክብረ አበው ነገሥት በተሰኘው መጽሐፋቸው ቅዱስ ላሊበላ የሠራቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጠ ሥራዎቻቸው፣ ምሳሌያቸው፣ ኅብራቸው፣ ምስጢራቸው ጽርያ አርያምን፣ መንበረ መንግሥትን፣ ሰማይ ውዱድን ይመስላሉ ብለው ጽፈዋል።
እነዚህ እጹብ ድንቅ ኾነው የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት የዓለም ዓይን ሁሉ ማረፊያ ናቸው። ብዙዎች በሮሃ በአንድ አለት ላይ የተሠሩትን የቅዱስ ላሊበላን ረቂቅ ሥራዎች ሊያዩ ወደ ሮሃ ይመላለሳሉ። ባዩዋትም ጊዜ ደስ ይሰኛሉ፣ አብዝተውም ይደነቃሉ።
በእነዚህ የረቀቁ አብያተ ክርስቲያናት አጸድ ሥር የሚከወነው ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ታይቶ የማይጠገብ፣ ተሰምቶ የማይሰለች ነው።
የአብያተ ክርስቲያናቱ ካህናት እንደ በረዶ የነጣውን ጋቢያቸውን ለብሰው፣ ያማረውን ልብሰ ተክህኖ ደርበው በአጸዱ ሥር ሲያመሰግኑ ግሩም ድንቅ ነው።
በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ድንቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከሚፈጸምባቸው ጊዜያት መካከል ወረኃ ጽጌ አንደኛው ነው። በዚህ ጊዜ ወደ ሮሃ ያቀና፣ በቤተ ማርያም አጸድ ሥር የተገኘ ሁሉ ዓይኑ መልካም ነገርን ታያለች፤ የሚያስደንቀውን ሥርዓት ትመለከታለች፤ ጀሮውም ምድራዊ የማይመስለውን ጥዑም ድምጽ ትሰማለች፤ አፍንጫውም ከሽቶ ሁሉ የላቀውን ያማረውን ማዕዛ ታሸትታለች።
የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ ወረኃ ጽጌ የአበባ ጊዜ ማለት ነው። ይህም ጊዜ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ነው። በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የቅድስት ድንግል ማርያም ስደት ይታሰባል ይላሉ።
በዚህ ጊዜ ማሕሌተ ጽጌው ድንቅ ኾኖ ይደረሳል።
በቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ደግሞ በሚያስደንቅ ሥርዓት ይፈጸማል። ማሕሌተ ጽጌው በቤተ ማርያም ይፈጸማል። ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ በምስጋና ያነጋሉ፤ በዚህ ወቅት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንት በአንድነት በቤተ ማርያም ይገናኛሉ፤ መላእክት በሰማይም በአንድነት አምላካቸውን እንዳመሰገኑ ሁሉ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንትም በቤተ ማርያም በአንድነት ያመሰግናሉ ይላሉ።
በወርኃ ጽጌ በቅዱስ ላሊበላ የሚፈጸውም ሥርዓት ሊታይ የሚገባው ድንቅ ነገር ነው፤ በልደት ወደ ላሊበላ የሚመጡ ምዕመናን እና ጎብኚዎች በጽጌም ወደ ላሊበላ መምጣት አለባቸው፣ የሚያስደንቀውን ሥርዓት መመልከት አለባቸውና ነው የሚሉት።
ጽጌን በላሊበላ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ልክ ልደትን በላሊበላ ተብሎ እንደሚከበረው ሁሉ ጽጌን በላሊበላ ለማክበር መሥራት ሀገርን ይጠቅማል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
