
በአማራ ክልል እየተገነቡ ከሚገኙት አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት እየተገነባ ይገኛል። ግንባታው በ13 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈም ነው።
ትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍል፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ቤተ መጽሐፍት እና ሌሎች ልዩ ልዩ የአገልግሎት መሠረተ ልማቶችን አካትቶ የያዘ ነው።
በዚህ ዓመት ግንባታውን በማፋጠን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ርብርብ እየተደረገ ነው። በዚህ መሠረትም በ2019 የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎችን አወዳድሮ ለመቀበል ትምህርት ቢሮው ጥሪ አድርጓል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ ለአሚኮ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታው በተሻለ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ሕንጻዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እና ዋና ዋና መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉለት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
በቅርቡም የመምህራንን እና የአሥተዳደር ሠራተኞችን በፍጥነት በማሟላት በ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 200 ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ምክትል ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ አካባቢም የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሚገኝ በመኾኑ የጎደሉ ነገሮችን ከኮሌጁ ጋር በማስተሳሰር ተማሪዎችን ለማስተማር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል።
ይህም ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከመጠበቅ እና የአንድ ዓመት የትምህርት ጊዜን ከማባከን ይልቅ በተጠናቀቀው ግንባታ እያስተማሩ መቆየት ተመራጭ መኾኑ ታምኖበት የተወሰደ ርምጃ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜም ቀሪውን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ከሥራ ተቋራጮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
