
በአማራ ክልል ለጌጣጌጥ፣ ለኮንሥትራክሽን፣ ለኢንዱስትሪ እና ለኀይል ማመንጫ የሚያገለግሉ የተለያዩ የማዕድን ሃብቶች ይገኛሉ። ግራናይት፣ ሲርካ፣ ኦፓል፣ ወርቅ፣ ሳፋየር፣ ኢምራልድ፣ የድንጋይ ከሰል እና ሌሎች የማዕድን ሃብቶች ደግሞ ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው።
ከዘርፉ የሚገኘውን ገጸ በረከት በመለየት፣ በማጥናት እና በማከማቸት ከመጠቀም አንጻር ያለው እንቅስቃሴ ግን ይበልጥ መሥራት እንደሚገባ የሚያሳይ ነው። ክፍተቶችን በመለየት የማዕድን ሃብቶችን በማልማት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ደግሞ የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ በትኩረት እየሠራ ነው።
የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ኀላፊ ኀይሌ አበበ የማዕድን ሀብቶች ላይ ጥናቶችን በማከናወን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት በማዕድን ሀብት 131 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ገልጸዋል። ክልሉ በ2018 በጀት ዓመት 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርቧል።
በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ 2 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ እየተሠራ ነው። በሩብ ዓመቱ 431 ኪሎ ግራም ወርቅ መሠብሠቡንም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። አማራ ክልልን በወርቅ ምርት ቀዳሚ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ከእስትራቴጂክ ማዕድናት ጋር በተያያዘ ወርቅ፣ ድንጋይ ከሰል፣ ሊትየም፣ ኮፐር እና ብረት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል። የውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዲወጡም ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። የክልሉ መንግሥት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የማዕድን ላብራቶሪ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመገንባት አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል። የማዕድን ጥናት ናሙናዎችን ወደ ውጭ መላክ ቀርቶ በሀገር ውስጥ ይመረመራሉም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
