ከ1ሺህ 500 በላይ ዜጎች በነጻ የዐይን ሕክምና ተጠቃሚ ሊኾኑ ነው።

8
👁የደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዐይን ሕክምና ማዕከል ከ”ኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት” ጋር በመተባበር በደብረ ብርሃን እና በአካባቢው ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የዐይን ሕክምና ሊሰጥ ነው። አሚኮ ያነጋገራቸው የደብረብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
የዐይን ክፍል አስተባባሪ ሲስተር ዋጋየ መከታ እንደነገሩን ታካሚዎችን ቀድሞ የመለየት ሥራ ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸውልናል። ይህም እስከ ሕዳር 11/2019 ዓ.ም እንደሚቀጥል አመላክተዋል። አሁን ላይ በየወረዳዎች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ልየታው
እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ዋናው የሕክምና አገልግሎት ደግሞ ከሕዳር 14/ 2019 ዓ.ም እስከ ሕዳር 24/ 2019 ዓ.ም ይሰጣል ብለዋል። በዘመቻው የሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና፣ የትራኮማ እና ሌሎች ተያያዥ የዐይን ሕመሞች፣ የዐይን ቧንባ መደፈን እና ዐይን ላይ
የሚወጣ ስጋ ማስወገድ ሕክምና እንደሚሰጥም ተናግረዋል። የዐይንን ዕይታ ማስተካከል የሚያስችሉ እና ሌሎች የላቁ የዐይን ሕክምና አገልግሎቶች እንደሚሰጡም ገልጸዋል። በዚህ የሕክምና ዘመቻ ቢያንስ 1ሺህ 500 ዜጎችን የዐይን ብርሃን መመለስ ዋናው ግብ ተደርጎ
ተይዟልም ብለዋል።ይህ ሰፊ የሕክምና ዘመቻ በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ታክመው መዳን ያልቻሉ (ከሕፃን እስከ አዋቂ ማንኛውንም የዐይን ችግር ያለበትን ሰው) ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መኾኑንም አስረድተዋል። ከሆስፒታሉ እና ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተዘረጋው
ይህ አሠራርም የእነዚህን ታካሚዎች የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የመጠለያ እና የመድኃኒት ወጪዎች ሙሉ በሙሉ በመሸፈን የሚከናወን እንደኾነም ተናግረዋል።ሆስፒታሉ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲህ ዓይነት የዐይን ሕክምና እንደሚሰጥ እና ልምዶች እንዳሉትም አንስተዋል። ለረጂም ዓመት
ሳይተያዩ የቆዩ እናት እና ልጆች፣ የትዳር አጋሮች የተያዩበት አጋጣሚ ሰፊ እንደነበረም አስታውሰዋል።በዘመቻው ከሀገር ውስጥ የዐይን ሕክምና ከሚሰጡ ተቋማት እና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ የተቀናጁ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል። ይህም የባለሙያዎች የዕውቀት
ሽግግር የሚደረግበት ትልቅ መድረክ ይኾናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል።ይህንን መልዕክት ገንዘብ አጥተው በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች እንዲሰሙት እናድርግ ብለዋል በመልዕክታቸው።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሚና በሀገር ግንባታ ላይ
Next articleበኤሮ ስፔስ ዘርፍ ሀገሩን ለማስጠራት ርዕይ የሰነቀው ባለ ምጡቅ አዕምሮ