በኤሮ ስፔስ ዘርፍ ሀገሩን ለማስጠራት ርዕይ የሰነቀው ባለ ምጡቅ አዕምሮ

9
🇪🇹
ተማሪ አማኑኤል እንቢያለ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፋግታ ለኮማ ወረዳ ተወልዶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዚሁ አካባቢ በሚገኘው አዝማች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በ8ኛ ክፍል ፈተና ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት አማካኝነት ተወዳድሮ በማለፉ የሁለተኛ
ደረጃ ትምህርቱን በደሴ ይሁኔ ወልዱ አዳሪ ትምህርት ቤት የመማር ዕድል አግኝቷል። በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር ዓቀፍ ፈተና ወስዶ 586 ነጥብ 9 በማስመዝገብ አስደናቂ ውጤት አምጥቷል። ይህ ውጤትም በክልሉ ሁለተኛው ኾኖ ተመዝግቧል።
ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤትም በአማራ ክልል መንግሥት ሰርትፍኬት እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለት እውቅናን አግኝቷል።
የአርሶ አደር ልጅ እንደኾነ የገለጸው ተማሪ አማኑኤል “ቤተሰቦቼ ዋጋ ከፍለው እንዳስተማሩኝ የእነርሱን ውለታ ለመክፈል ስል በጽናት ማጥናቴ
ለስኬታማነቴ ምክንያት ኾኗል” ይላል። በወቅቱ ውጤቱን ሲያየው የቤተሰቦቹን ፍላጎት በማሳካቱ እሱም ኾነ ቤተሰቦቹ ደስተኛ መኾናቸውን ነው ለአሚኮ የተናገረው። የመምህራንን ድጋፍ በአግባቡ መጠቀም፤ ጊዜን ከፋፍሎ በዕቅድ ማንበብ፤ በቂ ረፍት ማግኘት እና ከፈተና በፊት ጥያቄዎችን
በራስ አቅም እያወጡ በስፋት መለማመድ ውጤታማ የሚያደርጉ ስልቶች መኾናቸውን ነው የገለጸው። በቀጣይ በኤሮ ስፔስ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ አጥንቶ ሀገሩን ማገልገል እንደሚፈልግ ሀሳቡን አጋርቶናል። ይህንን ሕልሙን ለማሳካት ይረዳው ዘንድም በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል።
✍️ ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከ1ሺህ 500 በላይ ዜጎች በነጻ የዐይን ሕክምና ተጠቃሚ ሊኾኑ ነው።