የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሚና በሀገር ግንባታ ላይ

12
🇪🇹
አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ከቤተሰብ ወጣ በማድረግ በማኅበረሰባዊ ኑሮ ውስጥ ማሠማራታቸው ራሳቸውን እንዲችሉ፣ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብሩ እና ከልዩ ልዩ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በጋራ መኖርን እንዲለማመዱ በማድረግ ጠንካራ ስብዕና እና የሕይወት መሠረት የሚጥሉ ናቸው።
እንደ እንግሊዞቹ ኤተን እና ሀሮው ያሉ የአዳሪ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ተማሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያሥተዳድሩ፣ በቁጠባ እና በሥርዓት እንዲመሩ፣ የጊዜን አስፈላጊነት ተረድተው እያንዳንዱን ደቂቃ ለውጤት እንዲጠቀሙ ያስገድዳቸዋል።
በተቋማቱ ውስጥ ያለው ጥብቅ የዲሲፕሊን ማዕቀፍ የተማሪዎችን ልዩነት በማቀናጀት የቡድን መንፈስን፣ በሰላም አብሮ መኖርን፣ የመደማመጥ እና የመከባበር እሴቶችን በተግባር ያጎለብታል።
የሎውረንስ ኮልበርግ የሞራል እድገት እና የማኅበራዊ መስተጋብር ጽንሰ-ሀሳቦች እንደሚጠቁሙት ወጣቶች ከምቾት ቀጣናቸው ወጥተው በተቋማት ውስጥ ሲለማመዱ የሞራል አቅማቸው፣ የሲቪክ ብቃታቸው እና ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እጅጉን እንደሚያድግ ያሳያሉ።
አማራ ክልልን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋፋት ትኩረት የተሰጣቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ከአካባቢያዊ ውስንነት አውጥተው ሰፋ ባለ ሀገራዊ አውድ ውስጥ እንዲያድጉ ያደርጋሉ።
ስልቱ ተማሪዎች በፈተናዎች እና በኀላፊነቶች ጊዜ የሚፈጠሩ ጫናዎችን በብቃት እንዲቋቋሙ፣ ውሳኔዎችን በራሳቸው አቅም እንዲወስኑ እና ለወደፊት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መሪነት ብቁ እንዲኾኑ ያስችላል። ለሀገር ግንባታ ሲባልም ይህ አካሄድ ማኅበራዊ መከባበርን የሚያሰፍኑ፣
ብሔራዊ መግባባትን የሚገነቡ እና የሀገሪቱን የሰላም እና የልማት አቅጣጫ በብቃት ሊወስኑ የሚችሉ አርዓያነት ያላቸው ምሁራንን ለማፍራት ዋነኛው መሠረት ነው።
✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሕዳሴ እና የባሕር በር፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት እና የሕልውና ምሰሶዎች
Next articleከ1ሺህ 500 በላይ ዜጎች በነጻ የዐይን ሕክምና ተጠቃሚ ሊኾኑ ነው።