
አዲስአበባ፡- 26/02/ 2019 (አሚኮ) – 2ኛው የአፍሪካ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስአበባ መካሄዱን ቀጥሏል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ሴቶች አምራቾች፣ ፈጣሪዎች፣ መሪዎች እና የሰላም እና የልማት ምልክቶች እንጂ ዕርዳታ ጠባቂዎች አይደሉም
ብለዋል። በሴቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ማለት ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ማህበራዊ ትስስር እና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በመደመር ፍልስፍና እየተመራ በህብረት እና በጋራ የሁሉንም ዜጎች አቅም በማንቀሳቀስ
ልማታዊ ተጠቃሚነትን በፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከ2018 ጀምሮ ለሥርዓተ ፆታ እኩልነት የገባችው ቃል ኪዳን ሊለካ ወደሚችል የአመራር ውጤት ቀይራለች ያሉት ሚኒስትሯ፣ ሴቶች በካቢኔ ቦታዎች 50 በመቶውን በመያዝ እና የሀገሪቱን ከፍተኛ ተቋም
በመምራት ሚዛናዊ አስተዳደር መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ሴቶች አሁን ላይ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወክለዉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከማካተት አልፋ ሴቶች ፖሊሲዎችን በእኩልነት የሚቀርጹበት፣ ፈጠራን የሚመሩበት እና በሁሉም
የብሔራዊ ውሳኔ ደረጃዎች ትራንስፎርሜሽንን የሚመሩበት እድል ፈጥራለች ነው ያሉት። ሀገሪቱ ይህንን ተሞክሮ የፍጹምነት ማረጋገጫ አድርጋ ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት፣ አካታች የልማት ፍልስፍና እና ቀጣይነት ያለው እርምጃ በጋራ ሲሰራ የሚመጣዉን ለዉጥ ለማሳየት ለሌሎች
ታካፍላለች ብለዋል። ሴቶች እና ልጃገረዶች ለወደፊቱ ሙሉ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ ነጻ መሆን አለባቸው ያሉት ሚኒስትሯ ፣ በፖለቲካ አመራርነት ውስጥ በእኩል የሚወከሉበት፣ በኢኮኖሚ የሚጠቀሙበት እና መብትና ክብራቸውን የሚጠብቁ ተቋማትን እውን የምታደርግ አፍሪካን እንገንባ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
በቤተልሔም ሠሎሞን
