“የአራጣ ሥምምነት የበርካቶችን ቤት አፍርሷል”

14
በነጋዴዎች የባንክ ሂሳብ ላይ የሚደረግ የማንቀሳቀስ እገዳ እና የአራጣ ብድር በሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሕጋዊ ተግዳሮቶች ላይ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ የክልሉ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የባንክ ተቋማት እና አጋር አካላት በጋራ ውይይት
አካሂደዋል። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲጎለብት ለማድረግ ከ13 በላይ የመንግሥት ተቋማት በጋራ አቅደው እየሠሩ ነው ብለዋል። ከንግዱ ማኅበረሰብ እና ከተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት ወሳኝነት
አለው ነው ያሉት። የግብር ሥወራ ወንጀልን እና ድብብቆሽን ማስቀረት ሲቻል ኢኮኖሚ በሕግ እና ሥርዓት እያደገ እንደሚሄድም ገልጸዋል። የንግዱ ማኅበረሰብ መብት እንዲጠበቅ ያስችላልም ብለዋል። በንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የአራጣ ሥምምነት ወረቀቱን በማየት ብቻ
የሚለይ አይደለም ከወረቀቱ ጀርባ ማኅበረሰብን የሚጎዱ መጥፎ እሳቤዎችም ያሉት እንደኾነ ነው የተናገሩት። የአራጣ ሥምምነት የበርካቶችን ቤት አፍርሷል፤ የአራጣ ሥምምነትን ለማስቆም በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል። ብድር እና ወለድ ሕጋዊ አሠራር ያለው ፍትሐዊነትን
የሚያረጋግጥ በመኾኑም ከሕገ ወጥ ተግባር መራቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግዱ ማኅበረሰብ ድምጽ በመኾን ከፍትሕ አካላት ጋር ተቀናጅተው የንግድ ደኅንነትን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት
ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም መሐመድ (ዶ.ር) ማኅበረሰቡ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መብት እና ግዴታዎቹን እንዲወጣ ማስገንዘብ እና እንዲፈጽማቸው መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ነጋዴው የተሳለጠ ሥራን እንዲያከናውን በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።
ሕጋዊነትን በማስተማር በሕጋዊ መንገድ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መሥራት ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አሰፋ ወረታ (ዶ.ር) በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉ የአራጣ እና የባንክ ሂሳብ እግድ ላይ ችግሮችን
ለመቅረፍ ያለመ ውይይት መኾኑን ተናግረዋል። በንግድ ሥርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮች መፈታት ለኢንቨስትመንት መነቃቃት፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠር እና ለኢኮኖሚ ዕድገት መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በችግር ውስጥ ኾኖም ማልማት ተችሏል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next article“ሴቶች በፖለቲካ አመራርነት ውስጥ በእኩል የሚወከሉበት፣ በኢኮኖሚ የሚጠቀሙበት እና መብትና ክብራቸውን የሚጠብቁ ተቋማት እውን የምታደርግ አፍሪካን እንገንባ” የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሸዊት ሸንካ