
የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ክልላዊ የፓርቲ እና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። ባለፉት ሦስት ወራት የትላልቅ ፕሮጄክቶች መጠናቀቅ፣ የጣና ፎረም መካሄድ፤ የረጅም እና መካከለኛ ጊዜ ዕቅድ መዘጋጀቱ በመድረኩ ላይ
በስኬት የተነሱ ሃሳቦች ናቸው። በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በአንድ በኩል ሕግ የማስከበር በሌላ በኩል ደግሞ የልማት ተግባራትን ለማሳለጥ በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል። በተሠራው ተግባርም ሰላምን
በአንጻራዊነት መመለስ ተችሏል ነው ያሉት። በችግር ውስጥም ኾኖ ማልማት እንደሚቻል የታየበት መኾኑን አንስተዋል። ባለፉት ወራት የተሠሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት አበረታች እንደነበሩ ገልጸዋል። በግብርናው ዘርፍ ዘመናዊ የግብርና አሠራር መሠረት መጣሉንም
ተናግረዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ባለፉት ወራት ለሀገረ መንግሥት እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣሉን ተናግረዋል። በብሔር፣ በሃይማኖት እና በማንነት ስም የሚሠሩ
ከፋፋይ አጀንዳዎችን የማክሸፍ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ሀገራዊ ገዥ ትርክት ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል። በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መኾናቸውን ያነሱት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
