”የሚዲያ ተቋማትን አቅም በስልጠናና በሙያ ስነ ምግባር በማጠናከር ሀሰተኛ መረጃን መከላከከል ያስፈልጋል” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

13

 

አዲስአበባ፡- 26/02/2019 (አሚኮ) – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የሚዲያ የልህቀት ማዕከል አስመርቋል::

በምረቃ መርሀግብሩ የሚዲያ ተቋማትን አቅም በስልጠናና በሙያ ስነ ምግባር በማጠናከር፣ ሀገራዊ ብዝሃነትን እና ሰላምን የሚጠብቅ እንዲሁም የሐሰተኛ መረጃን መከላከል የሚችል የጋዜጠኝነት ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናግረዋል፡፡

አዲስ የተመረቀው የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል የግልም ሆነ የመንግስት ሚዲያ ባለቤቶችንና ባለሙያዎችን በማሠልጠን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት አምባሳደር ሬድዋን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀይማኖት ዘለቀ መንግስት የመገናኛ ብዙኃንን ዘርፍ ለማሻሻል ያሳየውን ቁርጠኝነት ተከትሎ በተደረገው የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻል፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን በዓይነትና በቁጥር ማስፋት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ የቁጥጥርና ድጋፍ ስራን በመስራት፣ ዘርፉን በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የጋራ ውይይት በማካሄድና ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የማስተካከል ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን ህዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ማዘጋጀት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።

በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6 መሠረት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ራሱን የቻለ የሚዲያ ስልጠና ማዕከል በማቋቋም የጋዜጠኞችን አቅም ለመገንባት በተሰጠው ኃላፊነት በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል በማቋቋም ለማስመረቅ መብቃቱን አብራርተዋል።

የማዕከሉ መቋቋም በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የሚስተዋለውን የዘርፍ ጋዜጠኝነት ክፍተት ለመሙላትና ጋዜጠኞች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ጥልቅ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደኾነ በመድረኩ ተገልጿል።

በቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

Previous article“የታዩ መልካም አጋጣሚዎችን እናጸናለን” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)
Next article“በችግር ውስጥ ኾኖም ማልማት ተችሏል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)