
በክልሉ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለግንባታው ዘርፍ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀው በደጀን ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተጎብኝቷል፡፡
የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር አስራት ኪዳኔ ፋብሪካውን በሦሥት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቅቆ ለማስረከብ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው በተያዘው ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል፡፡
ፋብሪካው በቀን 5 ሺህ ቶን የማምረት አቅም እንደሚኖረው የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ አሁን ላይ ከሦሥት ሺህ በላይ ዜጎች በፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ላይ እየተሳተፉ ስለመኾናቸው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የዓባይ ሰሚንቶ ፋብሪካ ግንባታው አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደረስ የክልሉ መንግሥት የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው በግንባታ ዘርፉ የሚስተዋለውን የግብዓት እጥረት ትርጉም ባለው ሁኔታ የሚፈታ ነውም ብለዋል፡፡ ፋብሪካው ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ምርት እንዲገባ ለማስቻል የክልሉ መንግሥት የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሠብሣቢ መላኩ አለበል የፋብሪካው አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 65 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የፋብሪካውን ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡
የዓባይ ሸለቆን ተንተርሶ የሚገኙ ጥሬ እቃዎችን ከፋብሪካው ጋር በማስተሳሰር የሲሚንቶ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ማምረት የሚችል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ ፕሮጀክት ስለመኾኑ አንስተዋል፡፡
ፋብሪካው ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሚንቶን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ የግንባታ ዘርፉ እና የሥራ ዕድል ፈጠራን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል፡፡
የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶች ትስስርን በማጠናከር በፌዴራል፣ በመንግሥት እና በባንኮች የብድር ድጋፍ በማመቻቸት የኢንዱስትሪ መሠረቶችን በማስፋት ረገድ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ግዙፍ ፋብሪካ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የገጠር እና ከተማ ልማትን ለማፋጠን፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ፋብሪካው አይነተኛ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡
የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ ማምረት ይሸጋገራል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
