
የአማራ ክልል የአሥተዳደር ዘርፍ ተቋማት የ2019 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸማቸውን እየገመገሙ ነው። በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ሰላም እና ደኅንነት፣ ሕግ እና ፍትሕ፣ የሕዝብ መብት ጥበቃ እና
መልካም አሥተዳደር ማስፈን የአንድ ተቋም ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የሁሉም ተቋማት የትብብር ውጤት መኾኑን አመላክተዋል። የዘርፍ አሠራር ስኬት የሚለካውም እያንዳንዱ ቢሮ የራሱን ዕቅድ በማሳካት ብቻ እንዳልኾነ ጠቁመዋል። ተቋማቱ በጋራ በመቀናጀት የሰላም፣ የፍትሕ እና
የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ሲመልሱ መኾኑንም ገልጸዋል። መድረኩ ዕቅድ በወረቀት ላይ ብቻ ሳይኾን በእያንዳንዱ ተቋም በባለቤትነት ተመዝኖ ውጤት እስኪመጣ መከታተል እና መተግበር የሚችለውን አፈጻጸም ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከአንድ ተቋም አቅም በላይ የኾኑ
ችግሮች በጋራ መፍትሄ እንዲያገኙ በጋራ መሥራት የሚያስችለው ቅንጅት እና የጋራ ኀላፊነትን ማዳበር ይገባልም ብለዋል። የስኬት መለኪያ በሪፖርት ብዛት ሳይኾን በተከናወኑ ተግባራት፣ በተፈቱ የሕዝብ ችግሮች እና በመጡ አወንታዊ ለውጦች መለካት አለበት የሚለው ውጤት ላይ
የተመሠረተ አሠራር ማዳበርንም ለስኬታማነት መሠረት አድርገውታል። የቀጣይ 90 ቀናት ጊዜ አጭር ቢኾንም የተመረጡ ዋና ዋና ሥራዎችን በብቃት፣ በሰው ኀይል እና በሀብት አጠቃቀም በመደገፍ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የሚገባበት ወሳኝ ወቅት መኾኑንም ገልጸዋል።
የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የፍትሕ አገልግሎቶችን ማሻሻል እና የሕዝብ ጥያቄዎችን በወቅቱ መመለስ፣ የተቋማትን ቅንጅት ማጠናከር፣ የሥራ ኀላፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ የቀጣይ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ኾነው ተመላክተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ተቋማቱ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን እያቀረቡ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
