
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ2019 በጀት ዓመት የሚገነባ 7ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት አስጀምሯል። ዛሬ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በተለምዶ ከኤላ ማደያ ከሚባለው አካባቢ ወይም ከመድኃኒዓለም ቤተ ክርስትያን እስከ አዲሱ የዓባይ ድልድይ የሚዘልቅ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኮሪደር ልማቱን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት ከተማዋን በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትኾን ታስቦ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት 19 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የኮሪደር ልማት
ሥራን በስኬት ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል። ከተማዋን በዘመናዊ ዕቅድ በማልማት ለነዋሪዎች እና ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ተሠጥቶ
እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የከተማ አሥተዳደሩ ባከናወናቸው የኮሪደር ልማት ሥራዎች በሰዓት የማይገደብ የሥራ ባሕልን አስገኝቷል፤ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የመጨረስ ልምድ አግኝተናልም ነው ያሉት። የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በሰዓት ሳይገደቡ ምሸት ድረስ ማገልገል
እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ዛሬ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከዚህ በፊት ያልተካተቱ የመሠረተ ልማት ዓይነቶች እንደሚካተቱበትም አንስተዋል። ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። ለዚህም ማኅበረሰቡ፣ ባለሃብቶች እና የሚመለከታቸው
ባለድርሻ አካላት ሁሉ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። ለአጠቃላይ ልማቱ መሠረት የኾነው ሕዝብም እንደተለመደው ሁሉ የሚጠበቅበትን ትብብር እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
