
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ።
ይህ ውሳኔ ከጦርነት አውድማ ወጥቶ ወደ ልማት፣ ዕድገት እና ማኅበራዊ ማገገም ለመሸጋገር ያስቻለ ትልቅ ተስፋ ነው። የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉት እነዚህ ወገኖች በይቅርታ እና በአዲስ አስተሳሰብ ታንጸው ለሀገር ግንባታ እየተዘጋጁ ይገኛሉ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ከተመለሱት ወጣቶች መካከል ተቀባ አየለ አንዱ ነው። ራሱን ጨምሮ 75 ወጣቶች በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ መግባታቸውን ያስታውሳል።
ቀደም ሲል በጫካ በነበሩበት ወቅት ሕዝቡን ላልተገባ ስቃይ፣ እንግልት እና በደል ሲዳርጉ መቆየታቸውን አልሸሸገም። ይሁን እንጂ ካለፈው ስህተት ተምረው የሕዝባቸውን ዕንባ ለማበስ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል እንደገቡ ተናግሯል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ ጋሻው ወልዴ በበኩሉ “ወደ ጫካ የወጣንበትን ዓላማ እንኳን በውል አናውቀውም፤ በግለሰቦች ግፊት እና ጫና ምክንያት የትግሉ ዓላማ ሳይገባን ለሦስት ዓመት ያህል በጫካ ቆይተናል” በማለት የነበረውን ሁነት በጸጸት ገልጿል።
ይህ የተሳሳተ መንገድም የወጣትነት ጊዜያቸውን እንደበላው እና በልማት ተሰማርተው ሃብት ማፍራት እና የሕዝባቸውን ሰላም መጠበቅ ሲገባቸው የገዛ ወገናቸውን በሰላም እጦት መበደላቸውን በጸጸት ተናግሯል።
የጫካው ትግል የሕዝብን ስቃይ ማራዘሚያ፤ የግለሰቦች ጥቅም ማስጠበቂ እና የእርስ በርስ መጠፋፊያ መኾኑን በመረዳት ወደ ሰላም እና ልማት ተመልሰናል ነው ያለው።
የትጥቅ እንቅስቃሴው የሕዝብን ስቃይ ከማራዘም የዘለለ ትርጉም የለውም፤ በተለይም ከታሪካዊ ጠላቶች ጎን ተሰልፎ የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት ማወክ ተገቢነት የሌለው የሀገር ክህደት ማሳያ ነው ይላል።
በመተማ ወረዳ በበጀት ዓመቱ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባደረጉት የማያቋርጥ ጥረት በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማማው አባተ ናቸው።
በቀጣይም የቀሩ ወጣቶች ወደ ሰላማዊው ሕይወት እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን እና የተመለሱትን ወጣቶች በንግድ፣ በእርሻ እና በልማት ሥራዎች ላይ የማደራጀት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መሪዎች የተስተካከለ የፖለቲካ አውድ በመፍጠር የጽንፈኝነት አስተሳሰብን መታገል እና ለልማት የተመቸ ምሕዳር መፍጠር አለባቸው ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት ያኮረፉት በይቅርታ መንፈስ እንዲመለሱ፤ ወጣቶች ከአርቆ አስተዋይነት ጋር ነገን እንዲቀርጹ እና ትውልዱ በምክር እንዲገነባ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
