አሕጉራዊ መድረኩን የሚመጥን አስተማማኝ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል” የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ

19
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጣና ፎረምን ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማካሄድ የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የኦፕሬሽናል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ዘለቀ አለባቸው ጣና ፎረም በርካታ ሀገራት የሚሳተፉበት አሕጉር አቀፍ መድረክ በመኾኑ ለክልሉም ኾነ ለሀገሪቱ በረከት ነው ብለዋል።
ፎረሙ በአስተማማኝ የሰላም ሁኔታ ውስጥ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ሰፊ የጸጥታ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ ለዚህ ሲባልም ለፎረሙ የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች የጋራ የዕዝ ሰንሰለት ተመስርቶ በሁሉም ቀጣናዎች የጸጥታ ሥምሪት መሰጠቱን አረጋግጠዋል።
ለፎረሙ የሚመጡ እንግዶች ያለምንም ስጋት ስብሰባውን እንዲያስኬዱ ብሎም በተፈጥሮ የታደለችው የባሕር ዳር ከተማ መዳረሻዎችን፣ በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ ደሴቶችን እና ጎርጎራን እንዲጎበኙ በሁሉም አቅጣጫዎች አስተማማኝ የጸጥታ ጥበቃ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።
ፎረሙ በስኬት እንዲጠናቀቅ በስፋት ከተሠሩት የሕዝብ ግንኙነት እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ባሻገር፣ ከወጣቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከጀልባ ማኅበራት እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የጋራ ውይይት በማድረግ የጸጥታ ሥራውን እንዲያግዙ መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።
ፎረሙ በተለያየ መልኩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመኾኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የፎረሙ አምባሳደር ነው ብለዋል።
የፎረሙ ተሳታፊ እንግዶች ቀድመው እየገቡ መኾናቸውን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ የሚመጡ እንግዶችንም ተቀብለን በኢትዮጵያዊ ባሕል እና እሴት እየተስተናገዱ መኾናቸውን አመላክተዋል።
ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል እንግዶች የኢትዮጵያን መልካም ስም እንዲወስዱ ለማድረግ ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ በመስጠት እና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለበትም አሳስበዋል።
እንግዳ አክባሪው የአማራ ክልል ሕዝብ፣ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ፣ የጸጥታ መዋቅሩ እና የፖለቲካ መሪው ሰፊ ዝግጅት ያደረገበት ሥራ በመኾኑ እንግዶች ፎረሙን በስኬት አከናውነው፤ በኢትዮጵያዊ ባሕል እና እሴት ተስተናግደው እንደሚሸኙም ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘለቀ አለባቸው አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ባሕር_ዳር_ጥቅምት_10_2019_ዓ_ም.
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የሕዝብ ስቃይ ይቁም ብለን ሰላምን መርጠናል” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች
Next articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ ሳይኾን የሉዓላዊነት እና የደኅንነት ጉዳይም ነው።