
የባሕር በር ጉዳይ ከኢኮኖሚ ጥቅም ባሻገር ከሀገር ሉዓላዊነት፣ ደኅንነት፣ ስትራቴጂያዊ አቅም እና ቀጣናዊ ተጽዕኖ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መኾኑን በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ምስክር ከተማ ገልጸዋል።
መምህር ምስክር እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር የነበራት ታሪካዊ ግንኙነት፣ በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የነበረው የንግድ እና የባሕር ትስስር እንዲሁም የዛሬው የባሕር በር ፍላጎቷ በታሪካዊ ሰነዶች፣ በዓለም ዓቀፍ ሕግ እና በዲፕሎማሲያዊ ማስረጃዎች በጥልቀት ሊመረመር ይገባል።
ይህም የሀገሪቱ የታሪክ አካል እና የአሥተዳደራዊ ባለቤትነት ማረጋገጫ መኾኑንም ያብራራሉ። በሴራ እና በፖለቲካ ሸፍጥ የባሕር በር ያጣንበትን አግባብ በግልጽ ማስረዳት እና መረዳት አስፈላጊ መኾኑን የጠቀሱት መምህሩ፤ ኾኖም ታሪካዊ ግንኙነቱን እና በቀደሙት ዘመናት የነበረውን የባሕር ተጠቃሚነት መነሻ በማድረግ ጉዳዩን በሕጋዊ ማስረጃዎች እና በዛሬው ዓለም ዓቀፍ የሕግ ማዕቀፍ መመልከት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም የ1982ቱ የባሕር ሕግ ስምምነት እና የወደብ አልባ ሀገራት የመጓጓዣ እና የባሕር ተጠቃሚነት መብቶችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ወሳኝ የውይይት መነሻዎች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር እንዲደርሱ እና በዓለም ዓቀፍ ንግድ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ የመጓጓዣ መብቶችን እና የትብብር መርሆችን ይደነግጋሉ።
ይሁንና የባሕር በር ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሌላ ሀገርን ግዛት በኀይል መያዝ ሳይኾን፤ በሕጋዊ ስምምነት፣ በጋራ ጥቅም እና በዘላቂ ትብብር ላይ መመሥረት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከሌሎች ወደብ አልባ ሀገራት ተሞክሮ በመማር፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረጉ የንግድ እና የመጓጓዣ ስምምነቶች የባሕር ተጠቃሚነትን ሊያሳድጉ እንደሚችሉ የገለጹት መምህር ምስክር፤ እነዚህ ስምምነቶች በፖለቲካዊ ለውጦች ሳቢያ እንዳይጎዱ ዘላቂነታቸው በሕግ የተጠበቀ እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ መኾን እንዳለበትም አብራርተዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ፤ ወደብ አልባ መኾን የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ ወጪ ከፍ ያደርጋል፣ በሌሎች ሀገራት ወደቦች እና የመጓጓዣ መስመሮች ላይ ጥገኝነትን ይፈጥራል፣ እንዲሁም በቀጣናዊ የደኅንነት ችግሮች ወቅት ሀገሪቱን ለተጋላጭነት ይዳርጋል።
ስለዚህ የባሕር በር ተጠቃሚነት ለኢኮኖሚያዊ ነፃነት፣ ለንግድ ተወዳዳሪነት፣ ለአቅርቦት ደኅንነት እና ለስትራቴጂያዊ ራስን መቻል ወሳኝ ነው።
በመኾኑም ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ሕጋዊ ማስረጃዎቿን በማጠናከር፣ የዲፕሎማሲ ጥረቷን በማሳደግ እና ከቀጣናው ሀገራት ጋር በንግድ፣ በወደብ አገልግሎት፣ በመጓጓዣ እና በደኅንነት ዘርፎች የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድም ትብብር መፍጠር ይኖርባታል ብለዋል።
ምሁራንም በጥናት ላይ የተመሠረቱ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረብ እንዳለባቸው እና ፖሊሲ አውጪዎች ደግሞ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ጥቅም በማስቀደም ለሰላማዊ እና ሕጋዊ መፍትሔ መሥራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ታሪክን ከማስታወስ ባለፈ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ጥቅም በሕግ፣ በዲፕሎማሲ እና በቀጣናዊ ትብብር ለማረጋገጥ የሚደረግ ስትራቴጂያዊ ጥረት መኾኑንም አስምረውበታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
