
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላም መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ታሪካዊ መሠረቱ የጀመረው በዓድዋ ድል መስዋዕትነት ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ጮራን በመፈንጠቅ ነው። ለዚህም ነው የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ “ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር በመኾኗ የአፍሪካ ነፃነት እናት ናት” ያሉት።
በኮሪያ ጦርነት የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ሠራዊትም ያሳየው ጀግንነት የሀገሪቱን የሰላም አስከባሪነት አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ አስመስክሯል።
ቀጥሎም በኮንጎ የተከናወነው ዘመቻ የኢትዮጵያንን አርበኝነት እና ለአፍሪካ አንድነት የነበራትን ጽኑ አቋም አሳይቷል።
በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሚና እጅግ ግዙፍ ነው። በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በቡሩንዲ፣ በኮትዲቯር፣ በላይቤሪያ እና በሩዋንዳ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ተከናውነዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት የሽብር ቡድኖችን አከርካሪ በመስበር ለሕዝብ እፎይታ ያስገኘ የሰላም ሠራዊት ነው። ኡሁሩ ኬኒያታ “እናት ሰላም ካላገኘች ቤተሰብም ሰላም ሊያገኝ አይችልም” በማለት ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ያላትን አስተዋጽኦ መስክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የሕይወት መታደግ እና የሌሎችን ሰላም የማስጠበቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰላም አስከባሪዎች ከሚያዋጡ ሀገራት አንዷ ናት። ሠራዊቱ ከማኅበረሰቡ ጋር በመልካም ግንኙነት በመኖር እና ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ የአፍሪካን አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
