“ስለ ኢትዮጵያ ጸንተዋል፤ ጠላቶቿንም አሳፍረዋል”

7
በሀገር ይጌጣል፣ በሀገር ደስታ ይታያል፣ በሀገር ይከበራል፣ በሀገር ይኮራል። ሀገር የሌላቸው በበዓዳን ሀገር ተንከራትተዋል፣ ሀገር የሌላቸው በወገን ፊት ማጌጥን፣ በዘመድ ፊት መደሰትን ናፍቀዋል፣ ሀገር የሌላቸው መዳረሻ አጥተው ተንከራትተዋል። ነጻነት ርቋቸው በባርነት ታስረዋል። ሀገር የሌለውን ያገኘ ሁሉ ይረግጠዋል፣ የተነሳ ሁሉ ይገፋዋል፣ ክብሩን ዝቅ ያደርገዋል፣ ሀገር የለሽ እያለ ያሳድደዋል።
ሀገራቸውን ያጡት፣ ነጻነታቸውን የተነጠቁት ቢጠማቸው የሚጠጡት፣ ቢርባቸው የሚጎርሱት፣ ቢደክማቸው የሚያርፉበት በሌለበት፣ ለዐይን ተስፋ በማይገኝበት ምድር እየተንከራተቱ የበረሃ ሲሳይ ኾነው ቀርተዋል።
ሀገራቸውን ያስከበሩት፣ ነጻነታቸውን ያስጠበቁት ግን በኩራት ተራምደዋል፣ የፈለጉትን አድርገዋል። ለሀገር ክብር ሲሉ የሞቱት፣ ለነጻነት ሲሉ የተሰዉት ልጆቻቸውን ባለ ሀገር አድርገዋል። በነጻነት ኖረው ነጻ ሀገር ነጻ ትውልድ አፍርተዋል። የኢትዮጵያ ጀግኖች ስለ ከበረች ሀገራቸው፣ ተስፋ ስለኾነች ሠንደቃቸው፣ በምንም ስለማይለውጧት ክብራቸው፣ ዝንፍ ስለማትል ወርቃማ ታሪካቸው ሲሉ ደም አፈሰሱ፣ አጥንት ከሰከሱ። በደማቸው ነጻነት፣ በአጥንታቸው ማንነት አፀኑ።
ኢትዮጵያ ኾይ አንቺን የነኩሽ ዕለት ጠላቶችሽ ወዮላቸው፣ ኢትዮጵያ ሆይ አንቺን የተዳፈሩት ምን ይኾን የሚያድናቸው? እያሉ ይነሳሉ። በኢትዮጵያ ላይ የተነሱትን ሁሉ ይመታሉ። ኢትዮጵያ ሆይ ብንከዳሽ የጠበቀሽ፣ ያከበረሽ፣ የከለለሽ፣ ያበረታሽ፣ ያፀናሽ፣ ከሁሉም ያስቀደመሽ፣ ሁሉንም የሰጠሽ፣ ለምስክርነት ያስቀመጠሽ አምላክሽ ይክዳን፣ መቀበሪያ አፈር ይንሳን እያሉ የሚነሱት ልጆቿ አስከብረዋት ኖረዋል።
በየዘመናቱ አያሌ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ተነስተዋል፣ ኢትዮጵያ የምትለውን፣ ከምንም በላይ ሲጠሯት የምትጣፍጠውን፣ ልብን እየነዘረች በሐሴት የምትሞላውን ስም ሊያጠፏት፣ ነጻነቷን ሊነጥቋት፣ ታሪኳን ሊያጠፉባት ተነስተዋል። ጦር ሰብቀው፣ ወታደር አዝምተዋል። በየወንዙ ዳር እየተማማሉ ሊወጓት ቋምጠዋል።
ጀግና እየወለደች፣ ጀግና እያሳደገች፣ በጀግና ትጠበቃለች እና ኾኖለት ያሸነፋት፣ ገፍቶ የጠላት፣ እንደ ምኞቱ ከታሪክ መዝገብ ላይ የሰረዛት፣ ያሰረዛት አልተገኘም። እናጥፋሽ ያሉት ጠፍተው፣ እንጣልሽ ያሏት ወድቀው፣ እናዋርዳት ያሉት ተዋርደው፣ እናሸንፋት ያሉት ተሸንፈው ይመለሳሉ እንጂ። እርሷ ከድል ላይ ድል እየጨማመረች በታሪክ መዝገብ ከፍ ትላለች። እርሷ ምቀኞቿን እየጣለች በአሸናፊነት ትራመዳለች።
ጠላት በተነሳባት ጊዜ ልጆቿ ከዳር ዳር ይጠራራሉ፣ ጠላት ተነሳበት ወደ ተባለበት አቅጣጫ በአንድነት እና በጀግንነት ይጓዛሉ። የእነርሱ የማሸነፊያቸው ምስጢር አንድነታቸው እና ፍቅራቸው ነውና በአንድነት እና በፍቅር ይገሰግሳሉ፣ በአንድነት ክንድ ይሰነዝራሉ፣ በአንድነት ክንድ ያደቅቃሉ፣ በአንድነት ክንድ ጠላቶቻቸውን ይጥላሉ።
ገብረወልድ እንግዳወርቅ “ማይጨው” በሚለው መጽሐፋቸው ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ስለሀገር የተናገሩትን ሲጽፉ “አንድነት እና ፍቅር ከሌሎች መሣሪያዎች ይልቅ ለሀገር መኩሪያ፣ ለነጻነት መጠበቂያ፣ ለሕዝብ መመኪያ የሚኾን ለጠላት የማይደፈር፣ ጥንካሬው ከምሽግ ሁሉ የሚበልጥ ዋና መከላከያ ነው። ጠላትን ለመከላከል የወንድማማች ፍቅር እና አንድነት ከሌለ መሣሪያ ብቻውን ምንም አይጠቅምም። ምንም እንኳን ልብ እና መሣሪያ የሚደጋገፉ ቢኾኑም፣ የልብ ብርታት እና አንድነት ከሁሉ የሚበልጥ መሣሪያ መኾኑን መዘንጋት የለብንም” ብለዋል።
ለነጻነት ከሁሉም አስቀድሞ ፍቅር እና አንድነት ይኖር ዘንድ ግድ ይላል። ፍቅር እና አንድነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻቸውን መትተዋል፣ ድል አድርገው ሠንደቃቸውን አውለብልበዋል። ፍቅር እና አንድነት የጠላት ጠመንጃ የማይጥሰው ጽኑ መዳኛ ነውና። “ነጻነት የሌለው ሀገር እና ሕዝብ ገንዘቡም ሀብቱም የእርሱ አይደለምና ተስፋ የሌለው ኾኖ ይቀራል። በገንዘብ እየተቀጠረ ከባዕድ መንግሥት ጋር ሀገሩን የሚወጋ ሰው በዚያው በተቀጠረበት ሥፍራ የተገዛ የሚባል ስም ወጥቶለት በከንቱ ከመሞቱ በቀር እናቱን ኢትዮጵያን መክዳቱ በሥራው ይገለጣል” ይላሉ።
ያለ ነጻነት ከመኖር በነጻነት መሞት ይሻላል እንዲሉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነጻነት እና ለሀገር የሚሰስቱት የለም። ጀግኖች ለነጻነት ሲሉ መከራውን ረስተው፣ ሞትን ንቀው በጀግንነት ታገሉ፣ ለእማማ ኢትዮጵያ ደማቸውን አፈሰሱላት፣ አጥንታቸውን ከሰከሱላት። በደማቸው አስከበሯት፣ በደማቸው ፍሳሽ አኮሯት፣ ዳግም ከጠላት በላይ አዋሏት፣ ስሟን ከፍ ከፍ አደረጉላት።
የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ሰይፉን ለሚያነሳ ሁሉ የሞቀ ድጋፋቸውን፣ ተዝቆ የማያልቅ ነዋያቸውን ከመስጠት አይቆጠቡም። አይዞህ በላት፣ እረፍት አሳጣት፣ የደም ምድር አድርጋት፣ ልጆቿን አናክስላት፣ ገዝግዘህ ጣላት ይላሉ። ኢትዮጵያ ትፈርስ ዘንድ ለሚሠሩት ገንዘብ ያጎርፋሉ። ስልት ይቀይሳሉ። የተከፈለው እና ሞኝ የላከው ባንዳም የጌቶቹን ትዕዛዝ ይፈጽም ዘንድ የተባለውን በሞኝነት ያደርጋል።
በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የተነሱ ባንዳዎች ለዓመታት ኢትዮጵያን አድምተዋታል። ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ ከአባቶቻቸው ሲወርሱ ባንዳዎች ደግሞ የባንዳነትን ታሪክ ከኢትዮጵያ ጠላት ወረሱ። በወረሱት የባንዳነት ታሪክ ዛሬም ድረስ እማማ ኢትዮጵያን ይወጓታል። ሰላም ውላ ሰላም እንዳታድር ጦር ያነሱባታል።
ኢትዮጵያ ግን ባንዳንም ባዕዳንንም ድል ትመታለች። ኢትዮጵያ እልፍ ጊዜ ተፈትናለች፣ ፈተናዎቿን ግን በድል ተሻግራቸዋለች። ፈታኞቿንም ጥላቸዋለች። እንዳይነሱ አድርጋ ሸኝታቸዋለች። ጠላቶች እንኳን መልዕክተኛ ልከው ራሳቸው መጥተው፣ ጦር አዝምተውም ኢትዮጵያን አላሸነፏትም። ወደፊትም አያሸንፏትም። ለምን ለሀገር ክብር ሞትን የሚንቁ ጀግና ልጆች አሏትና።
ጀግንነት እና ቃል ኪዳን የተቀበሉት የኢትዮጵያ ጀግኖች በኢትዮጵያ ላይ እግሩን ያነሳውን ለመቅጣት፣ በዱር በገደል፣ በተራራ በሸንተረር ይመላለሳሉ። ኢትዮጵያን ያስከብሯት ዘንድ በጀግንነት ከጠላት ጋር ይዋደቃሉ። የተሰጣቸው ቃል ኪዳን፣ የተቀበሉት አደራ የማይሻር ነውና በጀግንነት ኢትዮጵያን ይጠብቃሉ።
ሀገር የሚጠብቁትን ተከተሏቸው፣ እስከ ሞት ድረስም ውደዷቸው።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሰባት ነገሮች ስለጣና ፎረም፦
Next articleኢትዮጵያ ሁሌም ለጋራ ደኅንነት እና ሰላማዊ አብሮነት ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው።