ከጉባ እስከ ቀይ ባሕር የተዘረጋውን የተንኮል መረብ የሚበጣጥሰው የቀጣናው ጠንካራ ኀይል።

14
የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ ዕድገት ከውኃ ሃብቷ በተለይም ከዓባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ ነው። ይህም በታሪክም ኾነ በዘመናዊው ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ውዝግብ ፈጥሮ ቆይቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽን ከባሕላዊው የቅኝ ግዛት የውኃ ድርሻ ሞግዚትነት ሚናዋ ለመናድ ያስቻለ ስልታዊ ምዕራፍ ነው።
ግብጽ የኢትዮጵያን የውኃ ሉዓላዊነት እንደ ህልውና ስጋት የምታየው በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ ኢፍትሐዊ ስምምነቶችን ብቸኛ ሕጋዊ ማዕቀፍ አድርጋ በመቁጠር የራሷን ፖለቲካዊ የበላይነት ለማስቀጠል በመፈለጓ ነው።
በመሬት መራቆት፣ በአፈር እና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም በኃይድሮ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ያደረጉት ቤልጂየማዊ የጂኦግራፊ ምሁር እንዳሉት በውኃ ሀብት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሀገራትን ሉዓላዊነት እና የልማት አቅጣጫ የሚወስን ቁልፍ መሳሪያ ነው።
ግብጽ ኢትዮጵያ ዓባይን ለልማት እንዳትጠቀም ለማድረግ ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማትን እና የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ስትጠቀም መቆየቷ የዚሁ ስልት ማሳያ ነው።
አሁን በኢትዮጵያ ጂኦ-ኢኮኖሚያዊ አድማስ ላይ የተደቀነው የቀይ ባሕር ጉዳይ የዚሁ ስትራቴጂካዊ ጫና ቀጣይ ምዕራፍ ነው። የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት እጅግ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛቷን፣ እያደገ የመጣው ኢንዱስትሪዋን እና የጂኦ-ፖለቲካ አቀማመጧን የሚመጥን ዓለም አቀፍ ንግድን ለማሳለጥ የባሕር በር ስንክሳሯን መፍታት ይኖርባታል። ይህም ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቷ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከሕዝብ ብዛት እና ከኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎት አንጻር የማይቀር እና መሠረታዊ የህልውና ጉዳይ በመኾኑ በሰላማዊ ውይይት እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መፈታት አለበት።
ይሁን እንጂ በአፍሪካ ቀንድ እና በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ ኀይሎች እና ታሪካዊ ተቀናቃኞቿ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉት ጥረት ከዓባይ ግድብ ተቃውሞ ጋር ቀጥተኛ የርዕዮተ-ዓለም እና የጂኦ-ፖለቲካ ትስስር አለው።
በሮበርት ካፕላን (The Revenge of Geography) ትንተና መሠረት የምሥራቅ አፍሪካ እና የቀይ ባሕር ኮሪደር የዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ የደም ስር ነው። በመኾኑም ኢትዮጵያ በነፃነት በዚህ ቀጣና ውስጥ የባሕር በር ባለቤት መኾኗ የክልሉን የኃይል ሚዛን በእጅጉ ይቀይረዋል።
በኢትዮጵያ የተዘረጋው ቀይ ባሕር እንዳትደርስ የመከልከል ተንኮል የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ነፃነት እና ሉዓላዊ ዕድገት በአንድ ጊዜ የማክሸፍ ስልታዊ ሴራ ነው። ይህንን ሴራ በውል ተረድቶ ሰብሮ ለመውጣት ደግሞ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የመቆም እና የመታገል ቁርጠኛ የቤት ሥራቸው ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በውኃም ኾነ በባሕር በር ላይ ያላት መብት ድርድር የሚደረግበት ጉዳይ ሳይኾን የህልውናዋ ማዕከል ነው።
✍️ ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleባሕር ዳር የአፍሪካ መሪዎችን ለመቀበል አሸብርቃለች።
Next articleቡና እና የልብ ጤና ከጥናቶች፦