ባሕር ዳር የአፍሪካ መሪዎችን ለመቀበል አሸብርቃለች።

11
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ለአንድ ከተማ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የመሠረተ ልማት ግንባታ መሥፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በፎረሙ ለመታደም የሚመጡ እንግዶች የከተማዋን ገጽታ፣ የቱሪዝም መዳረሻ፣ ባሕላዊ ክዋኔዎች፣ የአለባበስና የአመጋገብ ሥርዓትን እና የተለያዩ አዳዲስ ገጽታዎችን ይመለከታሉ።
ይህም ከተማዋን የንግድ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል በማድረግ ሁለንተናዊ ጥቅሞችን ያመጣል። የተፈጥሮ ጸጋዎችን በጉያዋ አቅፋ የያዘችው የባሕር ዳር ከተማ በየዓመቱ የጣና ፎረምን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል ታስተናግዳለች።
ባለፉት ዓመታት በባሕር ዳር ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደው የጣና ፎረምም የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴን እያነቃቃ ይገኛል። የፎረሙ መካሄድ የከተማዋን ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና ባሕላዊ መገለጫዎችን ለዓለም እንድታሳውቅ ዕድል ይፈጥራል።
የባሕር ዳር ከተማ የጣና ፎረምን ማስተናገዷ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ለመገንባት፣ ስሟ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ በመልካም ጎን እንዲነሳ እና ጎብኝዎች ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ታላቅ መድረክ ነው።
በአፍሪካ ቀጣና በሰላም እና በሌሎችጉዳዮች ላይ የሚመክረው ጣና ፎረም በዚህ ሳምንት 12ኛውን የአፍሪካ ከፍተኛ መሪዎች መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ያካሂዳል።
ፎረሙ ባሕር ዳርን የቱሪዝም ኮንፈረስ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ገልጸዋል።
ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ያላቸው ሆቴሎችን፣ አሥጎብኝዎችን እና እንግዶች የሚዝናኑበት ጀልባዎችን ቀድሞ ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል። በፎረሙ ከፍተኛ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንደሚገኙ ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ባሕር ዳር በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ገጽታ እንዲኖራት በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
ከተቋማት ጋር በመኾን ከተማዋን ውብ፣ ጽዱ እና ለዕይታ ማራኪ እንድትኾን መሠራቱንም ነው የገለጹት። ጉባኤው የአፍሪካ ኢንቨስተሮች የባሕር ዳር ከተማን እና የክልሉን ጸጋ እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው፤ የውጭ ባለሃብቶች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ያስችላል ነው ያሉት።
እንግዶች መጎብኘት የሚፈልጉትን የመስህብ ስፍራ በነፃነት እንዲጎበኙ የሚያስችል በቂ ዝግጅቶች ተደርጓል ብለዋል። በባሕር ዳር ዙሪያ የሚገኙ መስህቦች ይጎበኛሉም ነው ያሉት።
የጣና ፎረም ከጥቅምት 13/2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል።
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“እርስ በእርስ በመዋጋት የሚገነባ ሀገር የለም፤ አሁን ሰላምን መርጠናል” የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ወጣቶች
Next articleከጉባ እስከ ቀይ ባሕር የተዘረጋውን የተንኮል መረብ የሚበጣጥሰው የቀጣናው ጠንካራ ኀይል።