
የሰላም ደወል ከተደወለ፣ የይቅርታ እና የፍቅር በሮች ከተከፈቱ ውለው አድረዋል። ትናንት የተዘራው የሰላም ዘር ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ በጎ ፍሬዎችን ማፍራቱን አላቋረጠም። አሁንም የሰላም እጆች አልታጠፉም፤ የሰላም ድምፆችም “ኑ በጋራ ሀገር እንገንባ፤ በሰላም እንኑር” የሚለውን ጥሪያቸውን አቀናጅተው ቀጥለዋል። ይህን የሰላም ድምጽ የሰሙ አካላትም ሰላምን ብቸኛ አማራጭ አድርገው በመምረጥ በውጤቱ ተጠቃሚ እየኾኑ ናቸው።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ከፍተኛ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ደርሷል፤ የሰው ልጅ ሕይወት ያለጊዜው ተቀጥፏል። ችግሩ ያላንኳኳው ደጅ አልነበረም፤ ሁሉም የጉዳቱ ገፈት ቀማሽም ኾኗል። ይህን ችግር የተረዱ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ በደስታ መቀበላቸውን ቀጥለዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም አማራጭ የተከተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በወቅቱ ትክክለኛ መንገድ መስሏቸው ወደ ጫካ በመግባታቸው ማኅበረሰቡን ለእንግልት ዳርገውት እንደነበር ያወሳሉ። የሕዝቡን ማኅበራዊ ትስስር እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አስተጓጉለናልም ይላሉ። በወቅቱ የሕዝብ ሸክም ኾነን፣ እኛም ተቸግረን ማኅበረሰቡንም ስናስቸግር ቆይተናል በማለት ያለፈውን ድርጊታቸውን በቁጭት ያስታውሳሉ።
አላስፈላጊ በኾነው የጫካ ትግል ሕዝብን መበደላቸው ትልቅ የሕሊና ቁስል ነው ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎች የሕዝብ ጥያቄ ደግሞ በጫካ በአፈ ሙዝ ሳይኾን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚመለስ መኾኑን ተረድተናል ነው ያሉት። “እርስ በእርስ በመዋጋት የሚገነባ ሀገር የለም፤ አሁን ሰላምን መርጠናል” ነው ያሉት። የሰላም አማራጭ በመቀበላቸው ደስተኛ ኾነው ደስተኛ ቤተሰብ እንዲመሩ መቻላቸውንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ መንግሥት ባመቻቸላቸው የሥራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውን በኢኮኖሚ እያጠናከሩ መኾናቸውንም ይናገራሉ። አንዳንዶቹ ወደ መደበኛ የመንግሥት እና የግል ሥራቸው በመቀላቀል ሕዝብን በማገልገል ላይ ናቸው። የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት። እርስ በእርስ በመዋጋት የሚያድግ ሀገር የለም፤ አንድ ኾኖ ቆሞ በማልማት ነው እንጂ ብለዋል።
አሁንም በጫካ የሚገኙ አካላት ያለፈውን ስህተት በመገንዘብ የቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ባደረጉት ንግግር ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ እና ሉዓላዊነቷ የተከበረች አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመገንባት ዕድል በእኛ እጅ ነው ብለዋል።
ለማንኛውም ፈተና የማትበገር የጸናች ሀገር መገንባት ይገባልም ነው ያሉት። በዚህም በጫካ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሰላም መንገድ በመምጣት እና ይቅርታን በመከተል ሀገርን እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ካለፈው ስህተት በመማር እና ሰላምን በመቀበል የምትፈራ፣ የማትደፈር እና ገናና ሀገር መገንባት እንደሚገባም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
