ኢትዮጵያ ሁሌም ለጋራ ደኅንነት እና ሰላማዊ አብሮነት ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው።

15
ጣና ፎረም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ባለሙያዎች በባሕር ዳር እየተገናኙ በአህጉሪቱ በሚደቀኑ ፈተናዎች ዙሪያ የሚወያዩበት መድረክ ነው። የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች እና የመፍትሔ ሃሳቦችም ይቀርቡበታል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቢኔ ጉዳዮች ኀላፊ አዳም ተስፋዬ እንደተናገሩት አፍሪካ በግጭቶች፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በኢኮኖሚ ተጋላጭነት እና በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነች ትገኛለች። ከእነዚህ ውሥብሥብ ችግሮች ለመሻገርም ጣና ፎረምን የመሳሰሉ መድረኮች እና የራሷ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል።
የጣና ፎረም የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን ተነሳሽነት፣ መሪነት እና ባለቤትነት በሚመሩ መፍትሔዎች እልባት የመስጠት መርህን እንደሚከተል አብራርተዋል።
እንደ ጣና ፎረም ባሉ መድረኮች የሚካሄዱ ውይይቶችም በባለ ብዙ ወገን ትብብር ላይ የተመሠረተ አካሄድን በመከተል ለዘላቂ ሰላም መፍትሔ የሚያመጡ ስለመኾናቸው ጠቁመዋል። ይህም ለመረዳዳት፣ የተቀናጁ እና የተባበሩ የሰላም ጥረቶችን ለማጠናከር እንዲኹም በአህጉሪቷ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም ሁሌም ለጋራ ደኅንነት እና ሰላማዊ አብሮነት ጽኑ እምነት አላት ነው ያሉት። ለዚህም የማይቋረጡ ጥረቶችን እያደረገች እንደምትገኝም ተናግረዋል። ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በመቃኘት ለዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት የሚኾኑ አማራጭ መንገዶችን ማሳየቷንም ተናግረዋል።
እያጋጠሙ ላሉት ችግሮችም ውይይት ዋነኛ መፍትሔ መኾኑን በተደጋጋሚ እያሳየች እንደምትገኝም ጠቁመዋል። በጣና ሐይቅ የተሰየመው ይህ መድረክ ጣናን እና ባሕር ዳርን የአፍሪካ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ምሁራን ለዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት አዳዲስ መንገዶችን የሚቀይሱበት ኾነው ዓመታትን እንዲዘልቁ አስችሏል።
ባለፋት 11 ዓመታት መድረኩን በስኬት ያስተናገደችው ባሕር ዳርም እንደወትሮው ሁሉ 12ኛውን የጣና ፎረም ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች።
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ስለ ኢትዮጵያ ጸንተዋል፤ ጠላቶቿንም አሳፍረዋል”
Next article“የኢትዮጵያ የደኅንነት ጋሻ”