“የኢትዮጵያ የደኅንነት ጋሻ”

38
ከ21ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የአንድ ሀገር ብሔራዊ ደኅንነት እና ጥንካሬ በዋናነት በታጠቁ ወታደሮች ብዛት እና በመሣሪያዎች ብዛት ይለካ ነበር። በአሁኑ ዘመን ደግሞ የሀገራት ብሔራዊ ደኅንነት መረጃን በመሰብሰብ እና በመተንተን፣ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል እና ቴክኖሎጂን ለሰላም ግንባታ በላቀ ሁኔታ በመጠቀም ላይ የተመሠረተ ኾኗል።
በዚህ ረገድ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ደኅንነት እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር፤ የውስጥ እና የውጭ ስጋቶችን ቀድሞ ለመለየት ስልታዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ እና የመተንተን ዋነኛ ተልዕኮ የተሰጠው ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ከፊት የሚጠቀስ ተቋም ነው።
ይህን ተቋም ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ኾኖ ሕጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በስትራቴጂያዊ የለውጥ ሥራዎች መልሶ የማደራጀት እና የማዘመን ውጤታማ ተግባራት ተከናውነውበታል። የተከናወነለት ፈርጀ ብዙ የሪፎርም ስምሪት ተቋሙን የቴክኖሎጂ አቅም የታጠቀ፣ በሙያዊ ሥነ-ምግባር የታነጸ እና ከአድሏዊነት የጠራ የደኅንነት ጋሻ እንዲኾን አስችሎታል።
በዚህም ተቋሙ የሀገራዊ ሉዓላዊነት ዋስትና መኾን ችሏል። ተቋሙ ከብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ እና ከዓለም አቀፍ የስለላ ድርጅቶች ጋር ስልታዊ ትብብሮች በመፍጠር በቀጣናው እና በአሕጉሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ መኾን መቻሉም ተመላክቷል።
በሀገሪቱ ሁሉም ጫፍ የሰው ኃይል በቦታው መሄድ ሳያስፈልገው የፌዴራል ተቋሙ ውስጥ ኾኖ ብቻ መከታተል እና መረጃ መሰብሰብ የሚቻልበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጅ የታጠቀው ተቋሙ ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ቀድሞ በማክሸፍ ረገድ ያሳየው ተጨባጭ ውጤት የለውጥ ሥራው ውጤታማነት ትልቁ ማረጋገጫ ኾኗል።
ባለፉት ዓመታት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና የውኃ ሙሌት ወቅቶች የተቃጡ የሳይበር እና የሽብር ጥቃቶችን ቀድሞ በማምከን ረገድ የላቀ ሚና መጫዎቱ የሚታወስ ነው። የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን የሕገ ወጥ መሣሪያዎች ዝውውርን ጥብቅ ክትትል በማድረግ እና በቁጥጥር ሥር በማዋል ረገድም ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ተቋሙ በቅርቡ በጸደቁት ማሻሻያ አዋጆች የኤርፖርት እና የአየር ትራንስፖርት ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ የመቆጣጠር እና የሀገርን ሉዓላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ የመገንባት ሰፊ ተልዕኮም ተሰጥቶታል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የኤርፖርት እና የድንበር አሥተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠረ የድንበር ቁጥጥር፣ የአቪየሽን ደኅንነት እና የኤርፖርት ቁጥጥር ያላት ሀገር መኾኗን አንስተዋል።
የተቀናጀ የኤርፖርት እና ድንበር አሥተዳደር ትራንስፎርሜሸን ፕሮግራሙ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ የደኅንነት ስጋቶችን በመረጃ አስደግፎ አስቀድሞ ለማወቅ እና ለመከላከል ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
ዛሬ ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ጥቃቶችን ከመከላከል አልፎ ስጋቶችን ቀድሞ በሚያክሽፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ተቋም መኾን ችሏል።
✍️ ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ ሁሌም ለጋራ ደኅንነት እና ሰላማዊ አብሮነት ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው።
Next articleበወገራ ወረዳ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቡድኖች ወደ ሰላም ተመለሱ።