
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በክፉም በኾነ በደጉ ጊዜ ለሀገራት ወዳጃዊ ግንኙነት ከፍተኛ ቦታ የምትሰጥ ሀገር ናት። ይህ የዲፕሎማሲ ታሪኳ በዓለም አቀፍ መድረክ ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ታላቅ ማኅደሯ ኾኗል።
ይህ ጥበብ በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ከሮም፣ ከግሪክ፣ ከፋርስ እና ከሕንድ ጋር በነበሩ የንግድ እና የፖለቲካ ትሥሥሮች ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነቷን ገና በማለዳው ነበር ያረጋገጠው።
የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚነገሩን በተለያዩ ዘመናት የነበሩ መሪዎቿ በመልዕክተኞች አማካኝነት በቃል እና በደብዳቤ ከአውሮፓ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች ጋር ያደርጓቸው የነበሩት ወዳጃዊ ግንኙነቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ችለዋል።
ይህ በቃል እና በደብዳቤ መልዕክቶች ጥንታዊ መሠረት ላይ የተገነባው የዲፕሎማሲ ሥርዓት ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊው ዓለም ስትሸጋገር ለገነባችው የውጭ ግንኙነት መዋቅር ዓይነተኛ መነሻ እንደኾናትም ነው የሚጠቀሰው።
ይህ የረጅም ዘመናት የዲፕሎማሲ ጉዞ በአጼ ምኒልክ መሪነት በተገኘው ታላቁ የዓድዋ ድል ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የኢትዮጵያን አይደፈሬነት በአደባባይ በማስመስከር ታላላቅ የአውሮፓ መንግሥታት በአዲስ አበባ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤታቸውን እና ኤምባሲዎቻቸውን እንዲከፍቱ እና ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ሀገር እንዲኾኑ አድርጓቸዋል።
በኋላም ኢትዮጵያ ሊግ ኦፍ ኔሽንን እንድትቀላቀል ብሎም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት ከመሥራች 51 ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሀገር እንድትኾንም አስችሏታል።
ይህም ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ኀላፊነት የሰጠ እና የዲፕሎማሲ ጥረቷን ከወትሮው ከፍ እንድታደርግ አቅም ኾኗታል። የአፍሪካውያን ነፃነት እና የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዋነኛ ማዕከል፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ እንድትኾን ያስቻላት ነጻ ሀገር መኾኗ እና በዲፕሎማሲው መስክ ያላት ተሰሚነት መኾኑን ምሁራን ይመሰክራሉ።
እንዲህ እና እንዲያ እያለ በትውልዶች መካከል የተሻገረው፤ በሉዓላዊነት እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተው የውጭ ግንኙነት መርሗ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ስትራቴጂያዊ ተፅዕኖዋን ማስከበር ችሏል።
ይህ የዲፕሎማሲ ጥበብ ዛሬም በተለዋዋጭ የዓለም ፖለቲካ ውስጥ የኢትዮጵያን ቁልፍ ተዋናይነት እያደሰ ይገኛል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጀምሮ እስከ አፍሪካ ኅብረት ለአፍሪካ አንድነት፣ ዕድገት፣ መብት እና ነጻነት ድምጽ ስትኾን የኖረችው ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲውን ሜዳ በጣና ፎረም ወደ ጓዳዋ ስበዋለች።
በዚህ አህጉራዊ ከፍተኛ የደኅንነት እና የሰላም መድረክ አፍሪካውያን ራሳቸው ስለራሳቸው ደኅንነት፣ ሰላም፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና አንድነት በነጻነት የሚመክሩበትን አውድ ፈጥራለች።
ተለዋዋጭ እየኾነ በመጣው የዓለም የጂኦፖለቲካ ዑደት የአፍሪካን ስልታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ትግሎች ሁሉ ከዚህ መድረክ በሚፈልቁ ሃሳቦች ይቀረጻሉ።
መድረኩ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካውያን መፍትሔ” የሚለውን ታሪካዊ መርህ በተግባር የሚተረጉም፤ በመስኩ ኢትዮጵያ ያላትን ሚና እና ተሰሚነት፣ አህጉራዊ መሪነቷን ለዓለም ይገልጣል። የነገዋን ብሩህ አፍሪካ በባለቤትነት ለመቅረጽ ኢትዮጵያ የማይደበዝዝ ቁርጠኝነቷን ታሳይበታለች ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
ከቀናት በኋላ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ለሚካሄደው የጣና አህጉራዊ ከፍተኛ የደኅንነት እና የሰላም ፎረም በርካታ ታላላቅ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተወካዮች፣ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ባሕር ዳር ይከትማሉ። ታዲያ ይህ አህጉራዊ መድረክ በእርግጥም ኢትዮጵያ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም በተግባር የምታስመሰክርበት ዓይነተኛ መድረክ ይኾናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
