የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃልኪዳን ቤተሰብ እና የተማሪዎች ደስታ

7
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው። በአቀባበሉ ላይ አሚኮ ያገኛት ተማሪ ሰማሐር ወልደ ዮሐንስ ጎንደር የእንግዳ ተቀባይ ማኅበረሰብ መኖሪያ መኾኗን ተመልክቻለሁ ብላለች።
ዩኒቨርሲቲው ከአጼ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ጀምሮ ባደረገው አቀባበል ደስተኛ መኾኗንም አንስታለች። ዩኒቨርሲቲውን ከጠበቀው በላይ እንዳገኘው የተናገረው ሌላው ተማሪ ብርሃኑ አምሃ ነው።
በዩኒቨርሲቲው ያለው የቃልኪዳን ቤተሰብ ትስስር የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን መልካም እንደሚያደርገውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ቁርጠኛ መኾናቸውንም አንስተዋል።
አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል ቀደም ብሎ የተማሪዎችን መኖሪያ ከማስተካከል ጀምሮ የትራንስፖርት እና መመገቢያ አዳራሽ የማዘጋጀት ተግባር ሲካሄድ መቆየቱን የነገሩን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሳሁን ተገኘ (ዶ.ር) አቀባበሉ በጥሩ መንገድ እየቀጠለ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ በትኩረት እንደሚሠራም አብራርተዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃልኪዳን ቤተሰብ ትስስር ባለፉት ዓመታት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል። ይህም ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮ ኾኗል ነው ያሉት።
ተማሪዎች በቃልኪዳን ቤተሰብ መተሣሠራቸው ለትምህርታቸው አጋዥ መኾኑን ጠቅሰዋል። በዚህ ዓመትም ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2019 የትምህርት ዘመን ከ2ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን እየተቀበለ መኾኑ ተመላክቷል። የተማሪዎች ቅበላ በቀጣይ ቀናት እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።
✍️ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከቃል እስከ አካል፦ ጣና ዳር የደረሰው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ።