
በአማራ ክልል በ2019 የምርት ዘመን 734 ሺህ 434 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክን በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዋለ
አባተ የመስኖ ልማት እንቅስቃሴው አርሶ አደሮችን ከዝናብ ጥገኝነች በማላቀቅ በምግብ ራስን ከማስቻል ባለፈ ሥራ አጥነትን በመቀነስ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።ሰፊ የገጸ ምድር እምቅ አቅምን በመጠቀም፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ገቢን ያማከለ ተግባራትን በመሥራት
ጠንካራ አርሶ አደሮችን መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።በዞኑ የተጀመሩ የመስኖ ልማት ግድቦች እንዲጠናቀቁ እና አዳዲስ የመስኖ ልማት አውታሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ ነው ብለዋል።የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) በአማራ ክልል 2 ነጥብ 2
ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ የመልማት አቅም ቢኖረውም እስካሁን በዘመናዊ መስኖ ማልማት የተቻለው አምስት በመቶውን ብቻ ነው ብለዋል።በክልሉ በ2019 የበጋ መስኖ ልማት ከ734 ሺህ 434 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ከ95 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል
በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም 400 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማልም ብለዋል። ከዚህም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ነው የገለጹት።ይህን ግብ ለማሳካት የግብርና ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት በትኩረት
ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት። የውኃ አቅምን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል ።የመድረኩ ተሳታፊዎች ለአርሶ አደሮች ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ያለን የውኃ አቅም በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ በመስኖ ልማት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
#የመደመር_መንግሥት !
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
