ታሪካዊ ጠላቶችን የሚያንበረክከው- የመከላከያ ኢንጅነሪንግ አስደማሚ ስኬት

6
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቴክኖሎጂን በመታጠቅ ብቁ ወታደራዊ ኃይልን መገንባት ችሏል። ሠራዊቱ የውስጥ ባንዳዎችን እና የሀገር ታሪካዊ ጠላቶችን በማንበርከክ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው ሰላምዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስቻለ ነው። በግዳጅ ላይ በሚሠማራበት ወቅት መብረቃዊ ጥቃትን በመፈጸም ድልን በመቀዳጀት ይታወቃል።
የሠራዊቱ የመፈጸም አቅም በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፣ በሰው አልባ ድሮኖች፣ በተምዘግዛጊ ጀቶች፣ የጸረ ድሮን ሥርዓትን እና የተለያዩ ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂዎች እንዲታጀብ በማድረግ በኩል የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ትልቅ ሚና አለው።
ተቋሙ ለሠራዊቱ የሚያገለግሉ ቀላል እና ከባድ ወታደራዊ ትጥቆችን በማዘጋጀት፣ በማደስ፣ በማሻሻል፣ በማዘመን፣ በወታደራዊ ደኅንነት ቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ የምርምር አቅምን በመገንባት፣ ለጦር መሣሪያዎች የሚያስፈልጉ ጥይቶችን እና ቁሳቁሶች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል።
የጦር ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን እና ምርቶችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመላክ የሚያስችል ዓላማን ሠንቆ እየሠራ ነው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከባድ መሣሪያቸውን በማደስ ወደ ኃይል እንዲገቡ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በደርግ ዘመን ላይ ተገዝተው ጥቅም ላይ ያልዋሉ፣ የተረሱ እና የተጣሉ የሀገር ሃብት የወጣባቸውን ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችን መልሶ በማደስ ጥቅም ላይ እንዲውል ተሠርቷል ነው ያሉት። በዚህም ከፍተኛ የኃይል አቅም እንዲኾኑ አስችሏል ብለዋል።
የማደስ ሥራዎቹ የመከላከያ ሠራዊትን ተልዕኮን የማሥፈጸም አቅምን የሚያሳድጉ ናቸው። ከኃይል ውጭ የነበሩ የሜካናይዝድ ጦር መሣሪያዎችን አዘምኖ ለግዳጅ ከማዘጋጀት ባሻገር በራስ አቅም የሚሠራ መኾኑ ከፍተኛ ወጭን የቀነሰ እንደኾነም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመከላከያ ሠራዊት ተቋም በኢትዮጵያውያን ሀብት የተገዙ፣ ጥቅም ሳይሰጡ በየቦታው የተጣሉ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን፣ ታንኮችን፣ መድፎችን፣ ሮኬቶችን “በሪቨርስ ኢንጅነሪንግ” ለማመን በሚከብድ መንገድ በማደስ ከፍተኛ አቅም መገንባቱን ተናግረዋል።
የተበላሹ ከባድ መሣሪያዎችን መጠገን፣ ማሻሻል ብቻ ሳይኾን ጥቅም ላይ እንዲውሉም አስችሏል ነው ያሉት። ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ተስፋ ሰጭ ተግባር መኾኑንም ጠቁመዋል።
የጦር መሣሪያዎችን ከመግዛት ወጥተን አሻሽለን የተኩስ አቅምን ከፍ አድርገን ማምረት እና ማስታጠቅ መቻላችን አስደማሚ ውጤት ነው ብለዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ በታንኮች፣ በመድፎች እና በሮኬት ውጤቶች አመርቂ ውጤት እንደምታስመዘግብ ተስፋ ሰጭ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። በሜካናይዝድ እና በአየር ኃይል እየታየ ያለውን ለውጥ ለማመን የሚከብድ አስደማሚ ውጤት ነው ብለዋል።
በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከባድ መሣሪያ እና በአየር ኃይል ከኢትዮጵያ ያለፈ እና ለሌሎች የሚተርፍ ሥራ እንተገብራለን ብለዋል። የመከላከያ ሠራዊት በአንድ ወገን ሀገርን ከጠላት እየተከላከለ በሌላ ወገን እየተመራመረ የሀገርን አቅም እያሳደገ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበተፈጥሮ የታደለች፤ በውበቷ የተደነቀች፤ለሁሉም የተመቸች።
Next article“በአማራ ክልል ከ734 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ይለማል” መስፍን አበጀ (ዶ.ር)