በተፈጥሮ የታደለች፤ በውበቷ የተደነቀች፤ለሁሉም የተመቸች።

10
ጣናን በራስጌዋ ተንተርሳ፤ ዓባይን በወገቧ ታጥቃ፤ በውብ ዘንባባዎቿ እንደ ሙሽራ ታጅባ፤ ቅርስን፣ ታሪክን፣ ጥበብን ባሕልን ከከተማዋ እስከ ገዳማት ሰንዳ ይዛለች። በተፈጥሮ የታደለች፤ በውበቷ የተደነቀች፤ ለእንግዶች የተመቸች፤ በጎብኝዎች የተመረጠች፤ በነዋሪዎቿ የከበረች፤ ውቧ የጣና ፈርጥ የውበት ሰገነት፤ ባሕር ዳር ከተማ።
ለከተማዋ ልዩ ገጸ በረከት የኾነው የጣና ሐይቅ በሰማያዊ ድምቀቱ ከከተማዋ ጋር ተዋሕዶ ልዩ ውበትን አጎናጽፏታል። በምሽት በሐይቁ ዳርቻ የሚኖረው ነፋሻማ አየር፣ በፀሐይ ግባት በሐይቁ ላይ የሚፈነጥቀው የውብ ቀለማት ትዕይንት በቃላት የማይገለጽ ድባብን ይፈጥራል፤ ልዩ ስሜትን ይቀሰቅሳል።
በሐይቁ ላይ የሚገኙት ዕድሜ ጠገብ ገዳማት እና ደሴቶች ለከተማዋ መንፈሳዊ እሴትን ጨምረውላታል፤ የጥበብ ማዕከልነቷን አስመስክረውላታል። በከተማዋ ሰፋፊ መንገዶች ዳርቻ የተተከሉ ዘንባባዎች መንገደኛውን ሁሉ ቤተኛ ያደርጉታል። በምሽት የኮሪደር መብራቶች ከውብ የእግረኛ እና አስፋልት መንገዶች ጋር ተዳምረው ለምሽት ሽርሽር ይጋብዛሉ።
በባሕር ዳር ጊዜን ማሳለፍ ከባሕርም ከየብስም የሁለት ዓለም ችሮታን የሚያጎናጽፍ፤ ልዩ የሕይዎት ገጠመኝን የሚያስተርፍ አጋጣሚን ይፈጥራል። ባሕር ዳርን “አድሮ አዲስ” ይሏታል፤ ተመችቷቸው የሰነበቱባት፣ በፍቅር የኖሩባት እና በስስት የተመለከቷት ሁሉ።
ከታላላቅ የምርምር ተቋማት እስከ አነስተኛ ማዕከላት፤ ከአካባቢያዊ የመስህብ ሃብቶች እስከ ድንቅ እና ታላላቅ ጸጋዎችን አቅፋ ይዛለች። ከዓለም ታላላቅ ከተሞች ጋር በእህትማማችነት እየሠራች በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣የትምህርት እና ባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) የትምህርት ከተማነትም ተመርጣለች። የምርምር እና የመዝናኛ ከተማ ለመኾንም በቅታለች።
ባሕር ዳር በደማቁ የሕዝብ እንግዳ ተቀባይነቷ በስፋት ትታወቃለች። ለእንግዶች የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችንም አሟልታለች። የዓለም አቀፍ መዳረሻነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ትላልቅ ሁነቶች፣ ከሀገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶች በብቃት የማስተናገድ አቅሟንም ገንብታለች።
ለእንግዶች የተመቹ ባለኮከብ ሆቴሎች፣ ሎጂዎች እና የመዝናኛ አማራጮችንም አሟልታለች። እንደ ሰማይ በተንጣለለው የጣና ሐይቅ ላይ እንግዶች እንዳሻቸው የሚዝናኑበት ከትናንሽ ባሕላዊ ታንኳዎች እስከ ዘመናዊ ፈጣን ጀልባዎች አመቻችታለች። ከዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ የዓለም ዓቀፍ ስታዲዬም ባለቤትም ኾናለች።
ባሕር ዳር በየጊዜው በውበት ላይ ውበት፣ በድምቀት ላይ ድምቀት እየጨመረች “የጣናዋ ንግሥት የውበት ሰገነት” እየተባለችም በብዙዎች ዘንድ ትሞካሻለች። ብዙዎችም “ፈጣሪ ለባሕር ዳር አዳልቷል” እስከማለት የሚደርስ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ። የውጭ ሀገር ዜጎች እና ዲፕሎማቶችም ስለውበቷ እና ስለ ምቾቷ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በአንድ ወቅት አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ክፍል አርክቴክቸራል ሴክሬታሪያት ሳላህ አሕመድ “ከተማዋን ለረጅም ጊዜ አውቃታለሁ፤ ውብ እና ማራኪ ገጽታ ያላት ምቹ ከተማ ናት” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትኾን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም መዳረሻ መኾን የቻለች ከተማ መኾኗን ተናግረዋል።
ባሕር ዳር ድሮም ውብ ናት አሁንም የበለጠ አበባ ኾናለች፤ አሸብርቃለች። ሰላሟን አስጠብቃ ለጎብኝዎች ተናፋቂ ኾናለች። ዛሬም ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ፣ እንግዶቿንም ለመቀበል ተዘጋጅታለች።
✍️በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቻይና ሳውዘርን አየር መንገድ የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ።
Next articleታሪካዊ ጠላቶችን የሚያንበረክከው- የመከላከያ ኢንጅነሪንግ አስደማሚ ስኬት