ከአዝጋሚነት ወደ ፈጣን የኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ!

8
ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃዎችን እሴት ሳትጨምር ወደ ውጭ የመላክ እና እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ከውጭ የማስገባት ልምዷን ልትገታ መኾኑን በየጊዜው የምታደርጋቸው ውጤታማ ሥራዎች ያሳያሉ።
ሀገሪቱ በሚቀጥሉት አምስት እና 10 ዓመታት ውስጥ በጥሬ ዕቃ መልክ የምትልካቸውን ምርቶች እሴት በመጨመር፣ ከውጭ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች የማስገባት ልምዷን በደረጃ እንደምትገታ ያለጥርጥር የሚያሳዩ ሥራዎች እየታዩ እንደኾነ በፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲቲዩት ውስጥ የኢኮኖሚ ከፍተኛ ተመራማሪው ጀማል መሐመድ (ዶ.ር) ይናገራሉ።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ በኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያዎች ተወስደው ሲታዩ ይህን የሚያሳዩ ሥራዎች እየተመለከቱ እንደኾነ ነው የሚጠቁሙት።
ሀገሪቱ በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ገንብታ ሥራ ያስጀመረችው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ለማሳያነት ተወስዶ ሲታይ ይህን የሀገሪቱን ታላቅ ርዕይ ያሳያል ነው ያሉት።
የመደመር መንግሥት ግራንድ ስትራቴጂ እና ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃዎቿን በአነስተኛ ዋጋ ልካ መልሳ በከፍተኛ ዋጋ የተዘጋጁ ምርቶችን የምትገዛበትን የኢኮኖሚያዊ አሠራር ማስቀረት እንደኾነ አስረድተዋል። ይህ ሥራ ይህንኑ ከሀሳብ የተሻገረ ሥራ በተግባር ሊያረጋግጥ የሚችል እንደኾነ ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጥጥ፣ ቡና እና ወርቅ የመሳሰሉ ጥሬ ዕቃዎችን በዝቅተኛ ዋጋ ከላከች በኋላ፣ ምርቶቹ ተቀነባብረው ወደ አፍሪካ ገበያ በብዙ እጥፍ ዋጋ ተመልሰው ይሸጣሉ ያሉት ተንታኙ ይህም የሀገሪቱ ሀብት እና አቅም በኢኮኖሚ ስሌት ሲታይ ምን ያክል ስትጎዳ ስለመቆየቷ ያሳያል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በ8 ዶላር የሚሸጥ ቡና በውጭ ሀገር ተቆልቶ እና ተዘጋጅቶ በስታርባክስ ከ30 ዶላር በላይ፣ በጣሊያን ደግሞ ወደ ኤስፕሬሶ ተቀይሮ እስከ 50 ዩሮ እንደሚሸጥ ጠቅሰዋል። ይህ ማለት ሀገሪቱ እያጣችው የነበረውን የኢኮኖሚ የሚያሳይ እና ብዙ እንድትሠራ የሚያስገነዝብ ነው ይላሉ።
እሴት የመጨመር አሠራር በወርቅ ብቻ ሳይኾን በማዳበሪያ እና በሌሎች ቁልፍ የማዕድን ዘርፎችም ተተግብሮ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ የጠቀሱት የኢኮኖሚ ተንታኙ የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ ሰፊ እንደኾነ እና ወደ ከፍታ እየተጓዘች መኾኗን የሚያሳይ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ፋብሪካው ከፍተኛ የኤክስፖርት አቅም እንደሚፈጥር የሚናገሩት ተመራማሪው በዓመት እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ኤክስፖርት የማድረግ አቅም እንደሚፈጥር እና ሀገሪቱን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትኾን የሚያስችል እንቅስቃሴ ነው ብለውታል።
ቀደም ሲል 1 ኪሎ ወርቅ ሲላክ 70 በመቶው ብቻ ወርቅ ተብሎ ቀሪው 30 በመቶ እንደ ቆሻሻ ይደፋ እንደነበር እና የሚደፋው አካል ደግሞ እንደ ብር ያሉ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ማዕድናት ያካተተ እንደነበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አንደበት መስማት እንኳን በኢኮኖሚ ዘርፍ ለሚመራመር ቀርቶ ለሌላውም ሰው እጅግ የሚያስቆጭ ጉዳይ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ባለፈው ዓመት ከተላከው ከ5 እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር የወርቅ ኤክስፖርት ውስጥ ይህ የማጣሪያ አቅም እና ሌሎችም ኢኮኖሚን የሚያሳድጉ ሥራዎች ተሠርተው ቢኾን ኑሮ ገቢው እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ነው ያስረዱት።
ከተሠራ ሀገሪቱን አሕጉራዊ የማዕድን ማዕከል በማድረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ሰፊ የአየር ተደራሽነት በመጠቀም ከሀገር ውስጥ አልፎ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚወጣውን ወርቅ በማሠባሠብ እና በማጣራት ግዙፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መፍጠር እንደሚቻልም ነው ያስረዱት።
ይህንን ዘመናዊ የማጣሪያ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ የሚያንቀሳቅሱት እና የሚያሥተዳድሩት በዘርፉ የሠለጠኑ ሀገር በቀል ባለሙያዎች መኾናቸው ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ የሚጨምረው እሴት በቀላሉ እንደማይታይ ነው የጠቆሙት።
በቀጣይም ኢኮኖሚውን ሊቀይሩ የሚችሉ መሠረታዊ የመሠረተ ልማቶችን ኢትዮጵያ መገንባት ከቻለች ዕድገቷ ተገማች ባልኾነ መንገድ ከፍ እንደሚል ነው የጠቆሙት።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ የባሕር በር ሕልውና – የታሪክ፣ የሕግ እና የጂኦግራፊ እውነታ
Next articleየኢትዮጵያ ታሪክ ማስቀመጫ ሳንዱቁ ጣና።