የኢትዮጵያ ታሪክ ማስቀመጫ ሳንዱቁ ጣና።

13
ጣና ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ ውበት፣ ተመስጦ፣ አርቆ አሳቢነት እና ደግነት መገለጫው የኾኑ እልፍ ሚስጥራትን በጉያው የያዘ የኢትዮጵያ ታሪክ እና የጥበብ መናገሻ ሐይቅ ነው።
በሐይቁ የሚገኙ ገዳማት ላይ ባሉ የብራና መጽሐፍት ተጽፎ እንደሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል ማርያም በገዳሙ የነበራትን ቆይታ አጠናቅቃ ስትመለስ “ፀአና በደመና” ወይም ደግሞ በደመና ጫናት ከተባለው ሃሳብ በመነሳት በጊዜ ብዛት “ጻና” የሚለው ቃል ተለውጦ ለአሁኑ የሐይቁ መጠሪያ “ጣና” መሠረት እንደኾነው ያስረዳሉ ። በጥንታዊ የግዕዝ ቋንቋ አገላለጽ “ጻና ሐይቅ” ይባል እንደነበርም የታሪክ ማስረጃዎች ይነግራሉ።
ጣናን የአቴናው ድራማ ጸሐፊ አስክለስ “መዳብ የተቀባው ሐይቅ የኢትዮጵያ ጌጥ” ብሎ ተቀኝቶለታል፡፡ ባለቅኔው ሆሜርም “ከሌሎች የተለየ እና ጥርት ያለ የውኃ ባለቤት ነው ” ብሎ አሞካሽቶታል። ሀገሬው ደግሞ የሐይቁን ትልቅነት አሰቦ በመቆርቆር ይሁን በውኃ ላይ ውኃ የማለፍ ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋን ለመግለጽ “ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት፤ ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዘላለም ሄደበት” ብሎ ገጥሞለታል። ጣና ብዙ የጉማሬ እንስሳትን ስለያዘም “ጉማሬ ባሕር” ይባል እንደነበር የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ከ40 በላይ ወንዞች እና ጅረቶች ወደሱ የሚፈስሱለትም ነው።
ጣና ሐይቅ የተከማቸ ውኃ ብቻ አይደለም። ዓሳ እና አዕዋፍትን ብቻም አልያዘም፡፡ገዳማትን እና ቤተክርስቲያናትን ብቻም አላቀፈም። ቁጥራቸው በርከት ያሉ ደሴቶች መገኛ ብቻም አይደለም። ጣና በልብ አምሳያ የተሠራ፣ ከልብ የመነጨ፣ ትልቁን የዓባይ ወንዝ ያንሳፈፈ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ማስቀመጫ ሳንዱቅ፣ ዓለምን ንቀው በመመነን ስለ ሰው ልጆች፣ ስለ ዓለም እና ስለሀገር ሰላም የሚጸልዩ አባቶች እና እናቶች መሸሸጊያ በመኾን እስከ አሁን ድረስ የዘለቀ ነው።
ዓለምን ተሰናብተው እስከ ወዲያኛው ያሸለቡ የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት እና ቅዱሳን አባቶቾ እና መካነ መቃብር ማረፊያም ነው፡፡ በርካታ ዕድሜ ጠገብ ንዋየ ቅዱሳት፣ አስደናቂ የብራና መጻሕፍትም ይዟል። ጣና ለከፋው መተከዣ፣ ለጸሐፊው ሃሳብ ማጮለቂያ፣ ለድምጻዊው
መመሰጫ፣ ለፍቅር ጥንዶች ቃል መግቢያ፣ መዝናኛ፣ የአካባቢው ነዋሪ ሥራ ፈጣሪ (ተፈጥሮ የለገሰችው ኢንዱስትሪ)፣ የባሕር ዳር ጌጥ እና ግርማ ሞገስ፣ ባለውለታም ነው። ገና ያልተደረሰባቸው ምስጢራዊ ታሪኮች ያሉበት የኢትዮጵያውያን ሁሉ መስታወትም ነው።
በስፋቱ በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ጣና በአፍሪካ አራተኛው ሐይቅ ነው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ርዝመቱ 96 ኪሎ ሜትር፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ደግሞ 65 ኪሎ ሜትር ነው። ስፍቱ 3ሺህ 600 ሥኩየር ኪሎ ሜትር ነው። አማካይ ጥልቀቱ ደግሞ 9 ሜትር ነው፡፡ ይህ ሐይቅ ሦሥት አይነት የዓሣ ዝርያዎች መገኛ ነው። ቀይ ዓሣ፣ ነጭ ዓሣ እና ቀረሶ ዓሣ ይሰኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የነጭ ዓሣ ዝርያዎች በጣና ሐይቅ ብቻ የሚገኙ እና ሌላው ዓለም ላይ የማይገኙ ናቸው፡፡
በጣና ሐይቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዕዋፋት ዝርያዎች እንደሚገኙም መረጃዎች ያመላክታሉ። ከእነዚህ ውስጥ የነዋሪውንም ኾነ የጐብኝዎቹን ቀልብ የሚስቡት የተነደፈ ጥጥ መሳዬቹ ቆልማሚት (ፔልከን) የሚባሉ የአዕዋፍ ዝርያዎች ለሐይቁ ውብት አላብሰውታል። ተንሰራፍቶ የሚገኘው የደንገል ተክልም
(ፖፒረስ) ሌላኛው የጣና ጌጥ፣ የአካባቢው ነዋሪ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃ መስሪያ፣ ጌጥ እና ማስዋቢያ ነው። የአካባቢው ውበትም ከሐይቁ፣ ከመንደሩ፣ ከቀየው፣ ከሀገሩ እና ከአህጉሩ አልፎ የዓለም ቅርስ የብዝኀ ሕይወት መለያ ኾኗል።
ጣና ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማፈላለግ የተቋቋመው እና በአፍሪካ ኢኮኖሚ፣ ሰላም፣ ንግድ ትስስር እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ለሚመክረው አፍሪካዊው ነጻ ተቋም (ጣና ፎረም) ስያሜ ምክንያት ኾኗል፡፡ ይህ ፎረም ስያሜውን እንደያዘ ዘንድሮም ለ12ኛ ጊዜ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ ለመምከር ተዘጋጅቷል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከአዝጋሚነት ወደ ፈጣን የኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ!
Next articleአጀንዳ ከመቀበል ወደ መስጠት – የውጭ ጫናን ጥሶ የሚወጣው የኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ